Monday, February 27, 2012

ዕንቁ፣ ክርስቶስና ኢትዮጵያ በቅዱስ ኤፍሬም




ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
20/06/2004
መግቢያ
ለቅዱስ ኤፍሬም አንድ ወቅት ደቀመዛሙርቱ ዕንቁ ያመጡለታል፡፡ እርሱም ዕንቁውን በተመለከተ ጊዜ ሰማያዊ ምስጢር ተገለጠለት፡፡ ስለዚህም በዕንቁ ነገረ ሥጋዌውንና በጥምቀት ያገኘነውን ክብር ሰበከ፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ዕንቁን መሠረት አድርጎ ሰባት መዝሙራትን የደረሰ ሲሆን ከእነዚህ ድርሰቶቹ ውስጥ ለአሁኑ ስለኢትዮጵያና ስለንግሥት ሳባ እንዲሁም ስለኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የሚያወሳውን ሦስተኛውን መዝሙር ወደ አማርኛ መልሼዋለሁ፡፡

አንተ ዕንቁ ሆይ! ሰውነትህ ከልብስ የተራቆተ ነውና ራስህን መሰወር እንዴት ይቻልሃል? ነጋዴዎች አንተን ከማፍቀራቸው የተነሣ ከልብስ ተራቆቱ፤ ነገር ግን እነርሱ ከልብስ መራቆታቸው የአንተን ራቁትነት በልብሳቸው ለመክደን ሲሉ አልነበረም፡፡ አንተ ምንም እንኳ ከልብስ የተራቆትክ ብትሆን ከውስጥህ ሚፈልቀው ብርሃን ልብስህ ነው፤ መጎናጸፊያህም የብርሃኑ ነጸብራቅ ነው፡፡ ኦ አንተ ዕንቁ ሆይ! ግሩም የሆነው ባሕርይ እንዴት ድንቅ ነው!!
ከስህተት በፊት ሔዋን በገነት ሳለች ምንም እንኳ ከልበስ የተራቆተች ብትሆንም ልክ እንዳንተው ብርሃንን የተጎናጸፈች ውብ ነበረች፡፡ ከዚህ ልብሱዋ ያራቆትካት አንተ ሰይጣን ሆይ ርጉም ሁን፡፡ ጌታ ሆይ! ዕንቁው ያንተ ምሳሌ ነው ፤ አንተን ግን ይህ ሰይጣን ከዚህ ልብስህ ሊያራቁጥህ አይቻለውም፡፡ አሁን በገነት ሴቶች እንደዚህ ዕንቁ ብርሃንን ተጎናጽፈው የቀድሞዋን ሔዋንን መስለዋታል፡፡