በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
07/06/2005
ቅዱስ ጳውሎስ ርስት እንዴት እንደሚወረስ
ሲገልጥልን “ኑዛዜ ያለ እንደሆነ የተናዛዡን ሞት ማርዳት የግድ ነውና፡፡ ሰው ሲሞት ኑዛዛው ይጸናል ተናዛዡ በሕይወት ሲኖር ግን አይጠቅምም”
ይለናል፡፡(ዕብ.9፡16-17)ይህ ክርስቶስ እኛን የርስቱ ወራሾች ሊያደርገን እንደ ሞተ ለማስረዳት የተጠቀመበት ኃይለ ቃል ነው፡፡
ጥንተ
ነገሩን ስንመለከት እግዚአብሔር አምላክ ለአብርሃም “በእውነት እየባረክሁ አባርክሃለሁ እያበዛሁ አበዛሃለሁ ብሎ በሌላ በማንም
ሊምል ስላልቻለ በራሱ ማለለት፡፡”(ዕብ.6፡13-14) አብርሃም ይህን እግዚአብሔር የማለለትን መሐላ ይዞ ከልጆቹ ጋር በስደት
በባዕድ ሀገር ኖረ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲናገር “አብርሃም የተባለው ርስት አድርጎ ሊቀበለው ወዳለው ስፍራ ለመውጣት በእምነት ታዘዘ፡፡ ለእንግዶች እንደሚሆን በተስፋ ቃል በተሰጠው አገር በድንኳን
ኖረ የተስፋ ቃል አብረውት ከሚወርሱ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር እንደ መጻተኛ በእምነት ተቀመጠ፡፡ መሠረት ያላትን እግዚአብሔር የመሠረታትንና
የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበርና” ብሎናል፡፡(ዕብ.11፡8-10) ይህ መሐላ የአብርሃምን እምነት ይዘው የርስቱ ወራሾች ሊሆኑ ለተጠሩት
ሁሉ የሚሠራ መሓላ ነው፡፡