Tuesday, June 5, 2012

"አባታችን ሆይ" በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የመጨረሻው ክፍል


ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ 
29/09/2004
...እርሱ ንጉሣችን ከሆነ ማን ያስፈራናል? ጌትነቱን ማንም ሊቃወምና ሊያጠፋ የሚቻለው የለም ፡፡ አርሱ  “መንግሥት የአንተ ናትና” ሲለን እኛን የሚዋጋውን ለጊዜ እግዚአብሔርን የሚቋቋም የሚመስለውን ሰይጣንን ለእኛ እንዲገዛ አሳልፎ እንደሚሰጠን ሲያመላክተን ነው ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ እርሱ ከእግዚአብሔር ባሪያዎች አንዱ ነው ፤ ምንም እንኳ ከተዋረዱትና ለመተላለፋችን ምክንያት ከሆኑት ወገኖች ዋናው ቢሆንም ከላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ፈቃድ ካለገኘ በቀር በእግዚአብሔር ባሮች ላይ የማደር መብቱ የለውም፡፡ ስለምን  እኔ “ በባሮቹ ላይ” እላለሁ ፣ በእሪያዎች ላይ እንኳ በማደር እነርሱን አስቻኩሎና አጣድፎ ለማጥፋት ሰይጣን ከእግዚአብሔር ፈቃድን መቀበል የግድ አለበት (ማቴ.፯፥፲፬) በእንስሳት መንጋ ላይ እርሱ ካለፈቀደለት በቀር ከቶ ሊያድር ካልቻለ በሰው ልጆች ላይ እርሱ እግዚአብሔር ካልፈቀደ በቀር እንዴት ሊያድር ይችላል?


"አባታችን ሆይ"በቅዱስ ዮሐንስ አፈወረርቅ(ክፍል ዐራት)


“በደላችንን ይቅር በለን እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል” 
ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
29/09/2004
ከአእምሮ በላይ የሆነው ምሕረቱን ትመለከታለህን ? እጅግ ታላላቅ የሆኑትን ክፋቶቻችንን ካስወገደልንና የእርሱን ታላቅ የሆነው ስጦታውን ከሰጠን በኋላ ሰው ዳግመኛ ቢበድል እንኳ በደላችንን  ይቅር ሊል ዝግጁ እንደሆነ በዘዚሀህ  ኃይለ ቃል አስታወቀን፡፡ ስለዚህም ይህ ጸሎት የአማኞች ጸሎት ይሆን ዘንድ በቤተክርስቲያን የጸሎት ሥርዐት ላይ መጀመሪያ የሚጸለይ ጸሎት ሆኖ ተሠራ፡፡
 ሰዎች ተጠምቀው ክርስቲያን ካልሆኑ በቀር እግዚአብሔር አብን አባት ብሎ መጥራት አይችሉም፡፡ ይህ ጸሎት እንግዲህ አማኞች ሊፈጽሙትና ሁሌም ሊጸልዩት  የሚገባ ጸሎት ከሆነ ቅዱስ ሥጋውና ቅዱስ ደሙን ከተቀበልን በኋላ ብንበድልና ንስሐ ብንገባ ንስሐችን ዋጋ እንደማያጣ ግልጽ ይሆንልናል፡፡ እንዲህ ባይሆን ኖሮ እንዲህ ብለን እንድንጸልይ  ሥርዐት ባልተሠራለን ነበር፡፡ ስለዚህም እርሱ ኃጢአታችንን እንድናስብና ይቅርታን እንድንጠይቅ እያሳሰበን እንዲሁም እንዴት ምሕረትን ማግኘት እንደምንችል እያስተማረንና ሸክማችንን በቀላሉ እንዴት ማቅለል እንደምንችል እያሳየን በምሕረቱ አጽናናን፡፡