Wednesday, November 7, 2012

ቅድስት ኤልሳቤጥና ቅድስት ድንግል ማርያም በንጽጽር(ቅዱስ ኤፍሬም)



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
29/02/2005
አረጋዊቱ ኤልሳቤጥ የነቢያት ፍጻሜ የሆነውን ዮሐንስ መጥምቅን በእርጅናዋ ወለደች፤ ታናሽዋ ብላቴና ቅድስት ድንግል ማርያም ግን የመላእክትን ጌታ ወለደች፡፡ ከአሮን ወገን የሆነችው ኤልሳቤጥ በምድረ በዳ የሚጮኸውን የሰው ደምፅ ወለደች፤ የዳዊት ልጅ የሆነች ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ለሰማያዊው ንጉሥ ቃሉ የሆነውን ክርስቶስን ወለደችው፡፡ የካህኑ ዘካርያስ ሚስት የሆነችው ቅድስት ኤልሳቤጥ በጌታ ፊት የሚሄድ መልእክተኛውን ወለደች፤  የዳዊት ልጅ የሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ምድሪቱን የሚገዛት እግዚአብሔርን በሥጋ ወለደች፡፡  መካን የሆነች መኅፀን ሰዎችን ለንስሐ የሚያዘጋጅ ልጅን ወለደች፡፡ ድንግል የሆነች ማኅፀን ግን የሰው ልጆችን ኃጢአት የሚያስወግድ ልጅን ወለደች፡፡ ኤልሳቤጥ ሰዎችን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ ልጅን ወለደች፡፡ ድንግል ማርያም ግን በኃጢአት ያደፈችውን ምድር በደሙ የሚነጻ ልጅን ወለደችልን፡፡ በፅንሰት ታላቁ የሆነው ዮሐንስ ለያዕቆብ ቤት ብርሃን ሆናቸው፡፡ በፅነሰት ታናሹ የሆነው የድንግሊቱ ልጅ ክርስቶስ ግን ለዓለም ሁሉ የጽድቅ ፀሐይ ሆነ፡፡