በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
30/07/2004
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
የሕዝብና የአሕዛብ አባት ስለሆነው አብርሃም “አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤትን አደረገ አየም ደስም አለው”(ዮሐ.8፡56)
ብሎ ተናገረለት፡፡ አብርሃም የጌታን የማዳን ቀን በእምነት የተረዳው እግዚአብሔር ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛልሃለሁ ብሎ
በባረከው ጊዜ ነበር፡፡ ልጆቹ ቁጥራቸው ከሰማያውያን መላእክት ቁጥር እንደሚሆኑ ያለዘርዐ ብእሲ ከመንፈስና ከእሳት ተወልደው እሳታውያንና
መንፈሳውያን መላእክትን እንዲመስሉ በመረዳቱ አብርሃም አባታችን ሐሤትን አደረገ፡፡ ስለዚህም አብርሃም “የሰሌን ጫፍ ለጋውን ያማረ
የእንጨቱንም ፍሬ ይዞ በየቀኑ ዘንባባውን ይዞ ሰባት ቀን የመሠዊያውን ዙሪያ በመዞር አምላኩን አመሰገነ”(ኩፋሌ.13፡21-23)
በዚህም “አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤትን አደረገ” የሚለው ቃል ተፈጸመ፡፡ ይህን ይዘው እስራኤላውያን በየዓመቱ የዳስ
በዓልን የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ በቤተ መቅደስ ዙሪያ ሆነው በዓልን ያደርጉ ነበር፡፡(ዘዳ.16፡13) ነገር ግን እግዚአብሔር አምላክ
ለወዳጁ ለአብርሃም እርሱንና በእምነት እርሱን የመሰሉትን እንዴት እንደሚያድናቸው ሊያሳየውና እግዚአብሔርን የሚፈሩ ዋጋቸው ምን
እንደሆነ ሊያስተምርበት አባታችን አብርሃምን ልጁ ይስሐቅን እንዲሠዋለት አዘዘው፡፡