Saturday, July 28, 2012

“ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት አይሁን”(በቅዱስ ኤፍሬም)የመጨረሻ ክፍል



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
22/11/2004 ዓ.ም
ጌታችን “በሰገነት ላይ ያለ ወደ ኋላ አይመለስ”(ሉቃ.17፡31) በሚለው ኃይለ ቃሉ በእነርሱ ላይ ቁጣው ምንም የነደደ ቢሆንም የእነርሱን ጥፋት እንደማይወድ ያሳየበት ኃይለ ቃል ነው፡፡ “በዚያችም ወራት ለርጉዞች ለሚያጠቡ ወዮላቸው”(ማቴ.24፡19) ሲልም በጊዜው ስለፀነሱት ሴቶች ልጆቻቸው እየተናገረ ሳይሆን በሮማዊያን ጭንቅ የሆነ መከራን ትቀበላላችሁ ሲላቸው ነበር፡፡ ስለዚህም “ችግር በምድር ላይ በዚህም ሕዝብ ላይ ይሆናል”(ሉቃ.21፡23)ብሎ ተናገረ፡፡ በዚህም ምክንያት “ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ” በማለት ከዚህ መከራ እንዲድኑ ጌታችን አስጠነቀቃቸው፡፡ እንዲህም ሲል የጽድቅን ሥራ የማትሠሩባት ቀን ትመጣለች፡፡ በዚያች ዕለት መብራታችሁን ከዘይታችሁ ጋር ሳትይዙ እንዳትገኙ፤ ይህም ማለት ፍቅርን ከምጽዋትና ከንጽሕና ጋር ወይም እምነትን ከምግባር ጋር ሳትይዙ እንዳትገኙ ተጠንቀቁ በዚያች በመጨረሻዋ ሰዓት ለመብራታችን ዘይት እንፈልግ በማለት ያም ማለት የትሩፋት ሥራዎችን እንሥራ ብትሉ አይቻላችሁም፤ ምክንያቱም ጊዜው የሥራ ሳይሆን የፍርድ ጊዜ ነውና፡፡(ማቴ.25፡1-13) ስለዚህም ጽድቅን ሳትሠሩ ጊዜው ፈጥኖ እንዳይደርስባችሁና እንዳይፈረድባችሁ በጸሎት ትጉ ሲል “ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ተጠንቀቁ” አላቸው፡፡ በክረምት ፍሬ እንደሌለ በሰንበትም ሥራ የለም፡፡ ስለዚህም ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት አይሁን ሲል እምነትንና ምግባርን ሳትይዙ ድንገት ምጽአቱ እንዳይደርስባችሁ በጸሎት ትጉ ሲል ነው፡፡

“ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት አይሁን”(ትርጉም በቅዱስ ኤፍሬም)



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
21/11/2004 ዓ.ም
ተወዳጆች ሆይ ዛሬ ጌታችን “እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰችው ሥፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል”(ማቴ.24፡15) የሚለውን ኃይለ ቃል ትርጉም እንማማራለን፡፡ እንደሚታወቀው ኢየሩሳሌም ብዙ ጊዜ ጠፍታ በተደጋጋሚ መልሳ የተገነባች ከተማ ናት፡፡  ነገር ግን ይህ የትንቢት ቃል በኢየሩሳሌም የአምልኮው ሥርዐቱና በሌዋውያን ካህናት የሚቀርበው መሥዋዕት ፈጽሞ እንደሚቋረጥ የሚያስረዳ ኃይለ ቃል ነው፡፡ አስቀድሞ በነቢዩ ዳንኤል “የጥፋት ርኩሰት” የተባለውን አንዳንድ ተርጓሚያን  “ሮማውያን በቤተመቅደሱ እሪያ በመሠዋት ጭንቅላቱን ይዘው ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ እንደሚገቡና መቅደሱን እንደሚያረክሱት፤ ይህ በተፈጸመ ጊዜ የኢየሩሳሌም ጥፋት እንደቀረበ አንባቢው ያስተውል ሲል ነው ብለው ይተረጉሙታል፡፡(ፍጻሜው ግን ቅዱስ ጳውሎስ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ አዋጅ እየነገረ በእግዚአብሔር ቤተመቅደስ እስኪቀመጥ ድረስ አምላክ ከተባለው ሁሉ ሰዎችም ከሚያመልኩት ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርገው ተቃዋሚ እርሱ ነው” ብሎ የተናገረለት የሐሳዊው መሲህ መገለጥ ነው፡፡(2ተሰ.1፡4)