Tuesday, November 27, 2012

መስቀሉን ባሰብኩ ቁጥር



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
18/03/2005
የመስቀሉን ነገር ሳስብ እጅግ ድንቅ ግርምም ይለኛል፡፡ በጥምቀት በዚህ መስቀል ላይ ከክርስቶስ ጋር ተሰቀልን፡፡ በዚሁ መስቀል ላይ እርሱን ለበስነው፡፡ በዚሁ መስቀል ላይ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ በመሆን አባ አባ የምንልበትን የልጅነትን መንፈስ ተቀበልን፡፡ ስለዚህ ዲያቆን እስጢፋኖስ ክርስቶስን መስሎ “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያቁምና ይቅር በላቸው” ብሎ ጸለየ፡፡ በመስቀሉ ገነት ወደ ተባለው ክርስቶስ ገባን፡፡ ወደ ውስጥ ስንዘልቅ አማናዊው ዕፀ ሕይወት ወደ ተባለው ጎኑ በመቅረብ  ከፈሰሰው ክቡር ደሙ ጠጣን፤ መሥዋዕት አድርጎ ካቀረበው ሥጋውም በልተን ዘለዓለማዊ ሕይወትን አገኘንበት፡፡
 ትንሣኤአችንም የሚፈጸመው በቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነው፡፡(ዮሐ.6፡54) በዚህም ወደ መንግሥቱ ለዘለዓለም እንኖር ዘንድ ገባን፡፡ ቢሆንም አሁን ወደ መንግሥቱ መግባታችን ላይታወቀን ይችላል አልተገለጠምና፡፡ ሲገለጥ ግን ሕይወታችን ከእርሱ ጋር እንደሆነች እናስተውላለን፡፡(2ቆላ.3፡3) በተጠመቅንና ከቅዱስ ሥጋውና ከክቡር ደሙ በበላን ጊዜ ከእርሱ ጋር እንደተነሣን ያኔ እንረዳለን፡፡ ሕይወታችን እርሱ አብ ነው፣ ሕይወታችን እርሱ ክርስቶስ ነው፣ ሕይወታችን እርሱ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡እርሱን እኛ ስናመልከው እርሱ ደግሞ በእኛ ላይ ያድራል፡፡(ራእ.7፡15)