Thursday, February 9, 2012

ብርህት ዐይን



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
01/06/2004 
ውስጣዊ የሆነችው የነፍሳችን ዐይን መመልከት የምትችለው በእምነት ነው፡፡ በእምነት ዐይናችን እግዚአብሔር በመጽሐፍ እና በዐይን በሚታየው በዚህ ዓለም ሰውሮ ያስቀመጣቸውን ምሳሌዎችን መረዳት እንችላለን፡፡ ውጫዊዋ ዐይናችን በፀሐይ ብርሃን ታግዛ መመልከት እንድትችል ውስጣዊዋ  የነፍስ ዐይናችንም በእምነት ብርሃን  ታግዛ መንፈሳዊውን ዓለም ትመረምራለች ትመለከታለች፡፡ ነገር ግን ይህች የነፍስ ዐይናችን በኃጢአት ምክንያት ልትታወር ትችላለች፡፡ ውስጣዊዋ ዐይናችን በደንብ መመልከት እንድትችል ለማድረግ ንሕትና ጥርት ያለች መሆን አለባት፤ እርሱም ከኃጢአት ነው፡፡ ውስጣዊዋ ዐይናችን ንጽሕትና ጥርት ያለች ስትሆን ቅዱስ ኤፍሬም እንደሚለው “ብርህት ዐይን” ተብላ ትጠራለች፡፡ ይህች ቃል በቅዱስ ኤፍሬምና በሌሎችም የሶርያ ቅዱሳን አባቶች ዘንድ የምትዘወተር ቃል ናት፡፡
ውስጣዊው የነፍሳችን ዐይኖች የበሩ እንደሆነ ብቻ ነው የእግዚአብሔርን ሥራና ፈቃድ ማስተዋልና በሥነፍጥረትና በመጽሐፍ ቅዱስ ያሉትን ምሳሌዎችን መረዳት የምንችለው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት ፊታችንን እንደምንመለከትባቸው መስታወቶች ናቸው፡፡ ዐይኖቹ ብሩሃን የሆኑለት ሰው በእነርሱ ውስጥ እርሱ በእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል እንደተፈጠረ ይረዳባችኋል፡፡” (ቅዱስ ኤፍሬም)
የማየት ብቃታችንም ሊያድግ የሚችለው እምነታችን ያደገና የጨመረ እንደሆነ ነው፡፡ የነፍስ ዐይናችን በጣም ብርህት በሆነች ቁጥር እግዚአብሔራዊ እውነታዎችን በይበልጥ እየተረዳን እንመጣለን፡፡ አንዲት ነፍስ አንድን እግዚአብሔራዊ እውነት በተለያየ አቅጣጫ መረዳት የቻለች እንደሆነ የዚህች ነፍስ ዐይኖች ብሩሃን ናቸው ማለት ነው፡፡

“አንዲት አጥንት”



ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
01/06/2004
ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት የተጻፈ 


 “ከአዳም የጎን አጥንት የተፈጠረችው ሴት ከራስ ቅሉ አጥንት አለመፈጠርዋ በእርሱ ላይ እንዳትሰለጥን ነው ከእግሩም አጥንት ከአንዱ አለመፈጠሯ እርሷን መበደልም ይሁን መጨቆን እንዳይገባው ለማስተማር ነው፡፡ ነገር ግን ከጎን አጥንቱ ፈጠራት በክብር እኩል መሆናቸውን ለማሳየት፡፡ ይህ የጎን አጥንት ከክርኑ አካባቢ መሆኑ ሚስቱን ከጥቃት ሁሉ ይጠብቃት ዘንድ የባል ሚና መሆኑን ለማስገንዘብ ነው፡፡ እንዲሁም ከልቡም አጠገብ መፈጠሩዋ እርሷን ከልቡ ሊያፈቅራት እንዲገባው ለማመልከት ነው፡፡”(ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ)
ቅዱሳን እንዳስተማሩን እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ማዕከላዊ አድርጎ መፍጠሩ በዐይን የማይታዩትን መናፍስትንና የሚታዩ ፍጥረታትን ሁሉ እርሱ እንደፈጠረና ግዢያቸው እንደሆነ ምስክር እንዲሆነው ነው ይላሉ፡፡ ባጠቃላይ ሰው /Human beings/ የእግዚአብሔር የገዢነቱ ምልክት ነው፡፡
ስለዚህም አዳም በነፍስ ተፈጥሮው መልአካዊ ባሕርይ ሲኖርው በሥጋው ባሕርይው ደግሞ እንስሳዊ ባሕርይ ይንጸባረቅበታል፡፡ በዚህም መሠረት አዳም በሥጋው ባሕርይው ምክንያት ልክ እንደ እንስሳት ለመኖር መሠረታዊና አስፈላጊ ነገሮች የተባሉት ሁሉ ለእርሱ የተገቡ ሆኑ፡፡