Saturday, December 15, 2012

የሞቴ ማስታወሻ



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
06/04/2005
ሰው ማለት እንደ እግዚአብሔር ነው፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ከንቱ የሆነች አንዲትም ሰከንድ የለችም፡፡ ሰውም እንዲሁ ዘመኑን ሁሉ በጥንቃቄና ያለዝንጋዔ እግዚአብሔርን መስሎ ሊኖር ተፈጠረ፡፡ የሰው ደስታው እውነት፣ ጽድቅ፣ ቅን ፈራጅነት፣ ከእውቀት ያልተለየ ፍቅር ናቸው፡፡ እነዚህን በተመለከተ አዳም አባታችን፣ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና እርሱን በቅርበት ያወቁት ሐዋርያት ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ከጌታችንና ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርትም የምናስተውለው ሰው ሊጸድቅ የሚችለው ልቡን በቃሉ ሞልቶ የሥነ ምግባራችን ቁልፍ በሆነው ማስተዋል የተመላለሰ  እንደሆነ ነው፡፡ ይህን ግን ምናልባት በቀን ውስጥ ሁለት ደቂቃ ግፋ ቢል አምስት ደቂቃ ሰጥተን ብናስበው ነው፡፡ ይህም የሚሆነው ስለእግዚአብሔር እውቀቱ ካለው ነው፡፡ የሌለው ግን ዘመኑን ሁሉ እንደ ነዌ ያሳልፈዋል፤ አንድም ሰከንድ እንኳ እግዚአብሔርን የሚያስብበት ጊዜ የለውም፡፡ ከዚያ ይልቅ በዝንጋዔ ሆኖ በስሜቶቹ ፈቃድ እየተነዳ በኃጢአት ሲንቧቸር ይኖራል፡፡ ይህ የአብዛኞቻችን ሕይወት ነው፡፡