Friday, November 9, 2012

ከእነዚህ የወጣ ማንኛውም ትምህርት ኦርቶዶክሳዊ አይደለም!!!!



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
1/03/2005
ማንም ሊገነዘብ የሚገባው እውነት ይህ ነው፡፡ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን(oriental church) ትምህርት በሦስት መሠረታዊ እውነታዎች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ እነዚህም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ፣እግዚአብሔር በገለጣቸው እውነታዎች ላይ(በመንፈስ ቅዱስ)፣ ቤተክርስቲያን በተቀበለቻቸው በተለይ 1-5 ክ/ዘመን በተነሡ ቅዱሳን አባቶች ትምህርት ላይ ነው፡፡ ወይም በዐራት ሕግጋት ላይ የተመሠረቱ ናቸው እነዚህም 1. በተፈጥሮአዊ ሕግ (1ቆሮ.11፡14፤15) 2. በሕሊናዊ ሕግ ላ(ሮሜ.2፡14) 3. በመጽሐፋዊ ሕግና በመንፈሳዊ ሕግ ላይ(God revelation.1ቆሮ.2፡12-16፤)ናቸው፡፡
አንድ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት እነዚህን ማዕከል ያደረገ መሆን አለበት፡፡ከእነዚህ ዐራት መሠረታዊ የሕግ ምንጮች ጋር የተጣጣመ ሊሆን ይገባዋል፡፡ የእነዚህም አቀራረባቸው:- በእምነት(በቀጥታ በመቀበል፡፡ ይህ ከአእምሮ መረዳት በላይ የሆኑ እግዚአብሔር የገለጣቸውን እውነታዎችን ይመለከታል፡፡ ለምሳሌ የእግዚአብሔር ወልድን ከአብ መወለድን በተመለከተ፤የሥጋና የመለኮት ተዋሕዶን በተመለከተ፣ የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት፣ ወይኑ ወደ ደመ መለኮት የሕብስቱም ወደ ሥጋ መለኮት የመለወጥን ምሥጢርና ሌሎቹም ይገኙበታል) እና በምክንያት (logic or reason) ላይ የተመሠረቱ መሆን አለባቸው፡፡ ይህ በተፈጥሮአችንና በሕሊናችን ለተሠሩት ሕግጋት ትንታኔ የምንሠጥበት መንገድ ነው፤እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ እንድንረዳቸው የሆኑትንም ያካትታል፡፡

"መዝጊያውን አንኳኩ ይከፈትላችኋል" (የኅዳር ወር ምንባብ)



ትርጉም ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
(ቅዱስ ዮሐንስ ዘደማስቆ)
30/02/2005
ቅዱስ ዮሐንስ ዘደማስቆ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብን በተመለከተ እንዲህ ብሎ ጽፎልናል፡፡ “ከመንፈሳዊ እውቀት በላይ እጅግ አስደሳችና ጠቃሚ የሆነ እውቀት ምን አለ? እውቀት ለአንድ ለባዊት ነፍስ ብርሃኑዋ ነው፡፡ የእውቀት ተቃራኒ የሆነው አላዋቂነት ደግሞ በጨለማ ይመሰላል፡፡ የብርሃን አለመኖር ጨለማን እንዲያመጣ እንዲሁ የእውቀት ጉድለት ድንቁርናን ያመጣል፡፡ ስለዚህም አላዋቂነት ለእንስሳት እንጂ ለሰው ልጅ አይደለም፡፡ አንድ በተፈጥሮ የማወቅና የማገናዘብ ችሎታ የተሰጠው ፍጥረት ከእውቀት የራቀ ከሆነ ቁጥሩ ከእንስሳት ይሆናል፡፡ እውቀት ስል ግን እውነተኛውን እውቀት ማለቴ ነው፡፡ እውነተኛ እውቀትን የምናገኘው ከራሱ ከእግዚአብሔር ወይም እርሱ ካለመኖር ወደመኖር ካመጣቸው ፍጥረታት ነው፡፡ ሀሰተኛ እውቀት የሚባለው ግን በሥነፍጥረቱ ለእኛ ያልተሰጠ ወይም ጨርሶ ካልተፈጠረ ነገር የሚመነጨውን እውቀት ነው፡፡ እርሱ ሐሰተኛ እውቀት ይባላል፡፡