Saturday, August 11, 2012

ግሩም ድንቅ የሆነው ተፈጥሮ!!!



በዲ/ን ሽመልስ መርጊ
06/12/2004
በመንፈሳዊው ዓለም ሴት ልጅ ላስተዋላት ከገነትም ይልቅ የምትረቅ ናት፡፡ እኔ ስለሴት ልጅ ሳስብ በአግርሞት እሞላለሁ፡፡ አንድ ወቅት እግዚአብሔርን እንዲህ ብዬ ጠየቅሁት፡- ስለምን ነፍስን ለብቻዋ አልፈጠርካትም ? ስለምን ሥጋን ማኅደሯ አድርገኽ ፈጠርካት ?አልኹት፡፡ ለካ የነፍስ መዳኗና አምላኩዋን የማየቱዋ ምክንያት ሥጋ ነበረች!!! ይህም የተፈጸመው በሴት ልጅ በኩል ነው፡፡ ከእርሱዋ ክርስቶስ ከአጥንቱዋ አጥንት ከሥጋዋም ሥጋ  ሆኖ በአካል ተገለጠ፡፡ ስለዚህም ለእርሱ ከአጥንቱ አጥንት ከሥጋው ሥጋ ስለሆነች ሴት ተባለች፡፡ ሴት ማለት ደግሞ ክፋዬ ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም የአዳምን ባሕርይ ነስቶ በመወለድ የእርሱዋ ክፋይ(ልጅ) ሲባል እኛ ደግሞ ከእርሱ ከክርስቶስ ከአጥንቱ አጥንት ከሥጋው ሥጋው በመሆን የእርሱ ክፋዮች(ልጆች) እንባል ዘንድ በጥምቀት ከሞቱ ጋር ተባበርን፡፡ 
ሴቶች በሔዋን ሴት ሲባሉ፡፡ እኛ ወንዶች ደግሞ በክርስቶስ በተመሰለውና የአቤል ምትክ በሆነው ሴት በኩል ሴት ተባልን፡፡ ይህ ደግሞ ድንቅ ነው!!! 
ታዲያ ስለምን ሴት ልጅ ከነስሙዋ ድንቅ የሆነች ፍጥረት አትባል? ጥበብን የሚወድ እግዚአብሔር ሴት ልጅን የፍጥረት ጉልላት አድርጎ ፈጠራት፡፡ ከእርሱዋም ስሙ ጥበብ የሆነ ክርስቶስ ተወለደ፡፡ በክርስቶስም እኛ ክርስቲያኖች በጥምቀት ከአጥንቱ አጥንት ከሥጋው ሥጋ በመሆን ተወለድን፡፡ 
አዲሱም አፈጣጠራችን ሔዋን ከአዳም የተገኘችበትን አፈጣጠር ይመስላል፡፡ አዳም አንቀላፍቶ ሳለ ሔዋን ከጎኑ አጥንት ተገኘች፡፡ እንዲሁ እኛም ክርስቶስ በሞት እንቅልፍ አንቀላፍቶ ሳለ ከጎኑ በፈሰሰው ደም ተዋጅተን ከጎኑ በፈሰሰው ውኃ ነጽተን ዳግም ተፈጠርን (because we are members of His body of His flesh and His bones) እንዲል፡፡(1ቆሮ.12፡27) ታዲያ በመንፈሳዊ መረዳት ውስጥ ያለ ሰው እንዴት በሴት ልጅ ተፈጥሮ  አይደነቅ?

ከ20 በላይ የሆኑ መንፈሳዊ ጉራማይሌ አጫጭር ጽሑፎች




በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
05/12/2004
(እነዚህ ጽሑፎች በተለያዩ ጊዜአት ፖስት ያደረጉኋቸው ናቸው)
ክርስትናና ፍቅር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች
ፍቅርን የማያውቃት ክርስትናንም አያውቃትም ፡፡ ፍቅርን ሳያውቃት ክርስትናን አውቃታለሁ የሚል ሰው በእውነት እርሱ ሐሰተኛ ነው፡፡ በፍቅር ውስጥ ላለ ሰው ክርስትና ትፈቀራለች እንጂ አትከብድም፡፡ ክርስትና በፍቅር ውስጥ በሚገኝ ማስተዋል የምትመራ፣ የማታሰለች፣ ሁሌም ጥበበኛ የሆነች፣ ርኅሪት፣ ታጋሽ፣ አዛኝ፣ ሰው በሰው ማንነት ውስጥ ሆኖ ሰውነቱን እንዲያጣጥም የምትረዳ፣ ውስጡዋ ሰላም፣ ፍስሐ፣ ፍጹም ፍቅር የሞላባት፣ በተመስጦ የምታኖር የሰው ሰውነት ትርጉም ናት፡፡So let's build our faith on these, let's open our eyes with love and see all human beings with kindness. Don’t judge on others but appreciate their good deeds. Help each other without reward. In order to have pure mind, excellent thinking and healthy perspective, let us know God our lover and love all human beings on the eyes of God and love each other sincerely. Not in word but in deed.

ብሔርተኝነት
ክርስትና ዓለማቀፋዊት ናት ማንም በየትም ሀገር ይሁን ወደ እውነተኛይቱ የእግዚአብሔር መንግሥት በጥምቀት ከገባ በኋላ ክርስቲያን እንጂ የዚህ ሀገር የዚያ ሀገር አይባልም፡፡የተጠመቀ ሁሉ አንድ አካል ሆኖአል፡፡ የአንድ ሰማያዊት ሀገር ዜጋ ነው፡፡ለክርስቶስ ደግም አንዱ የአካል ክፍል ነው፡፡ይህን ቅዱስ ጳውሎስ ሀገራችን በሰማይ ነው ብሎ ይገልጽልናል፡፡ እጅ የምትሠራውን እግር አይሠራውም ዐይን የምትሠራውን ጆሮ አትሠራውም፡፡ ነገር ግን የአንዱ የአካል ክፍል ተግባር ሌሎችን የአካል ክፍሎች በአግባቡ እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ስለዚህ ብሔርተኝነት በክርስትና አይሠራም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ነው ያስተማረን፡፡ በአንድ እምነት ውስጥ ካለን የሌሎች እውቀትና ልምድ ለእኛ የጎደለንን ሲሞላልን የእኛ ደግሞ የሌሎችን ጉድለት ይሞላል፡፡ ስለሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃ በአንድ እምነት ሥር ያለን እርስ በእርሳችን ካልተመጋገብን ክርስትናን ኖርናት አያስብለንም አካለ ጎደሎዎች ነን እንጂ፡፡ ወገኖቼ ሆይ ብሔርተኞች አንሁን(Nationalist) ክርስትና ዓለማቀፋዊት ናት፡፡ ዓለማቀፋዊት የሆነችውን ብሔራዊት የምናደርጋት ከሆነ ራሳችንን ብንጎዳ እንጂ አንጠቀምም፡፡ ምክንያቱም ብሔርተኝነት በራሱ ምንፍቅና ነውና፡፡