በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
20/06/2005
ዛሬ አንድ የገጠመኝን ገጠመኝ ላውጋችሁ እንዲህ ነው፡- አንድ የልብ ወዳጄ “ለሆነ ጉዳይ እፈልግሃለሁ” ብሎ ወደ እርሱ በታክሲ አመራሁ የሥራ ቦታው ወደ መስቀል ፍራዎል አካባቢ ነበር፡፡ ሄድኩ በፍቅር ተወያየን ለእኔ ጥሩ አሳቢ ነበርና በእርሱ አምላኬን አመሰገንኹት፡፡ ከእርሱ ጋር ውይይቴን ከጨረስኩ በኋላ ከአምባሳደር ዐራት ኪሎ የሚለውን ታክሲ ይዤ ወደ ቤቴ አመራሁ፡፡
በመንገድ ላይ ሳለሁ ግን አንድ ወዳጄ ከክፍለሀገር ደወለልኝ፡፡ ስለ ግል ጉዳያችን ከተጠያየቅን በኋላ ወደ መጨረሻ ላይ ለመሆኑ “የአብርሃም ርስት ርስታችን” የሚለውን ምንባብ ተመለከትከውን? አልኩት ተመልከቼዋለሁ ግን ካነበብኩት ስለቆየሁ እስቲ ትንሽ አስታውሰኝ አለኝ፡፡ እኔም
“ለአብርሃም በራሱ ምሎ በመሐላ መካከል የገባውና በሞቱ ርስቱን ለአብርሃምና የአብርሃምን እምነት ይዘው ላሉት ሊያወርስ ሰው ሆኖ በመስቀል ላይ ራሱን ስለሰዋው እግዚአብሔር ቃል የሚያትት ነው”
ብዬ አስታወስኩት፡፡ እርሱም ፈላስፎች የሚያነሡትን ጥያቄ አስታውሶ እንዲህ አለኝ፡-
“ክርስቶስ እግዚአብሔር ከሆነ እርሱ ሞቶ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር ውስጥ ከነበረ በእነዚህ ሦስት ቀናት ውስጥ ዓለምን የሚመግባት ማን ነበር?
ብለው ፈላስፎች ይጠይቃሉና ስለዚህ ምን ትላለህ?
ብሎ ጠየቀኝ፡፡ ይህ ጥያቄ እንደው ለእነርሱ ከባድ መስሎአቸው ያነሱት ጥያቄ እንጂ ፍልስፍናን በማወቃቸው የጠየቁት ጥያቄ አይመስለኝም፡፡