ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
21/07/2004
“ቅድስት ድንግል ማርያም ስለልጁዋ ስለወዳጁዋ እንዲህ አለች፡- እኔ የተሸከምኩት ሕፃን እርሱ እኔን የተሸከመኝ ነው ፡፡ እርሱ ክንፎቹን
ዝቅ አድርጎ በእቅፎቹ ውስጥ አኖረኝ ፡፡ ከእርሱም ጋር ወደ ሰማየ ሰማያትም ተነጠቅኩ ፡፡ በዚያም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ
ለልጄ እንዲሆን ቃል ኪዳን ተገባልኝ ፡፡
ልጄን መልአኩ ገብርኤል ጌታዬ ብሎ ሲጠራው ሰማሁ ፣ ሊቀ ካህኑና አገልጋዩም
(ስምዖን አረጋዊ) እርሱን በእቅፉ ይዞ ስለእርሱ ትንቢትን ተናገረ ፡፡ ሰብአ ሰገል በፊቱ ወድቀው ሲሰግዱለት፤ ሄሮድስም ንግሥናዬን
የሚቀማ ሌላ ንጉሥ ተነሣብኝ ብሎ ሲርድ ተመለከትኩ ፡፡
ሙሴን አገኘዋለሁ ብሎ የዕብራዊያንን ሕፃናት ያስፈጀ ሰይጣን እርሱን
በመስቀሉ ጠርቆ የሚያስወግደውን ሕፃን ለመግደል ሽቶ ሄሮድስን መሳፈሪያው አድርጎ ሕፃናትን ለመግደል ተፋጠነ፡፡ ነገር ግን ጠላቶቹ የሆኑትን ሊያድናቸው የመጣው
ጌታ ወደ ግብፅ ተሰደደ ፡፡
ቀዳማይቱ ሔዋን በድንግናዋ የእፍረት ልብስ ለበሰች፡፡ ያንተ እናት
ግን በድንግልናዋ ለሁሉ የሚበቃውን የክብርን ልብስ ደረበች ፡፡ እርሱዋ ሁሉን የሚያለብሰውን ጌታ ውሱን የሆነውን ሥጋዋን አለበሰችው
፡፡