Thursday, May 25, 2017

ቅድስት እናቱን ለምን ኪዳነ ምህረት እንላታለን?

ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
19/09/2009

ክብር ለእርሱ ለወደደን ለኢየሱስ ክርስቶስ ይሁንና ብዙዎች ድንግል እናቱን ኪዳነ ምህረት ስንል ግራ ሲጋቡ አስተውላለሁ። በእርግጥም ግራ ቢጋቡ አይደንቅም ምክንያቱም ለመረዳት መጽሐፍ ቅዱስን ጠንቅቆ መረዳትና የመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ ይፈልጋልና። በብሉይ አማናዊው መሥዋዕት ከመሰዋቱ በፊት የቃል ኪዳኑ ታቦት ላይኛው ክፍል “የሥርየት መክደኛ” በእንግሊዘኛው ደግሞ “mercy seat` ይህም ማለት “የምሕረት ዙፋን"  ይባል ነበር። ምክንያቱም እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን በማድረጉ በታቦቱ  ራስ ላይ ተገልጦ ሙሴን ያነጋገረው ከካህናቱም መሥዋዕት ይቀበል የነበረው በዚህ ሥርየት መክደኛ ላይ ሆኖ ነበርና። ይህ መገለጥ ግን ከሰዎች ልጆች ጋር ፍጹም እርቅ መፈጸሙን የሚያሳይ አልነበረም። ነገር ግን በዚህ ሕዝቡ ይጽናናና ራሱንም ለበለጠ የትንሣኤ ሕይወት ያዘጋጅ ነበር። ምክንያቱም ይህ መገለጥ እግዚአብሔር ለአባታቸው ለአብርሃም የገባውን ቃል ኪዳን እንደማያጥፍ ማሳያ ሆኖአቸዋልና።
 በሰውና በእግዚአብሔር መካከል እርቅ የወረደው ግን ድንግል እናቱን የቃል ኪዳኑ ታቦት አድርጎ ሥጋና ደም ተካፍሎ ሰው ሲሆን ነው። ያኔ በሰውና በእግዚአብሔር በሰውና በመላእክት በሰውና በሰው መካከል የነበረው ጠብ ፍጻሜ አገኘ።  እርቅን ከሰው ጋር በተዋሕዶ ከፈጸመ በኋላ በሰው ልጆች ላይ ሰልጥኖ የነበረውን ዲያብሎስ ከድንግል እናቱ በተካፈለው ሰውነት በመስቀሉ ድል ነሳው። ድል መንሳትንም ለእኛ ሰጠን። ስለዚህ እርቅ የወረደልን ተስፋ መንግሥተ ሰማያት የተሰጠን እርሷንና ሥጋዋን ለራሱ የቃልኪዳን ታቦቱ በማደረግ ስለሆነ ድንግል እናቱን ኪዳነ ምህረት እንላታለን። ምክንያቱም ምህረትና እርቅ ለሰው ልጆች ሁሉ ሆኖአልና። 
እርሱ እግዚአብሔር ቃል ከእርሷ ከድንግል እናቱ ሥጋና ነፍስ ነስቶ ባሕርያችንን ለብሶ በእርሱም ለፍጥረቱ ተገልጦ በእኛ ላይ የተፈረደውን ፍርድ በራሱ ተቀብሎ ዲያብሎስን ድል ነስቶ በእርሱ ያመኑትን እርሱን ተስፋ የሚያደርጉትን ከቅዱሳን መላእክት ጉባኤ ደመራቸው፡፡ ያመኑትንም በጥምቀት እርሱን ለብሰን እንድንነሣ በማድረግ ከቅዱሳን ጉባኤ እንድንደመር አደረገን፡፡ ሰውነታችንን መቅደሱ በማድረግ ሕጉንም በመንፈስ ቅዱስ በልቡናችን ሰሌዳ ላይ ጻፈልን፡፡ እነዚህንና ሌሎች በረከቶችን ሊሰጠን የወደደው ከድንግል እናቱ በነሣው ሥጋና ነፍስ ነበር፡፡ ስለዚህም ድንግል እናቱ መንፈስ ቅዱስ አናግሩዋት “በእኔ ታላቅ ሥራን አድርጎአልና እንግዲህ ትውልድ ሁሉ ብጽዕት ይሉኛል” ብላ ከፍ አድርጋ ተናገረች፡፡ 
ስለዚህ ነው ኪዳነ ምሕረት መባልዋ፤ በእርሷ እርቅ ወርዶአልና። በነቢዩም “ ከዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔ አምላክ እሆንላቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል፡፡”(ዕብ.8፡10) የሚለው ቃል በእኛ የተፈጸመው በድንግል ማርያም ነው፡፡ እንዲህም ስለሆነ ቅዱስ ጳውሎስ “እናንተም በሕያው እግዚአብሔር መንፈስ እንጂ በቀለም አይደለም፥ ሥጋ በሆነ በልብ ጽላት እንጂ በድንጋይ ጽላት ያልተጻፈ፥ በእኛም የተገለገለ የክርስቶስ መልእክት እንደ ሆናችሁ የተገለጠ ነው”ብሎ ጽፎልናል፡፡ (2ቆሮ.3፡3)ይህን በማን አገኘነው ብንባል በክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ የድንግል እናቱን ሥጋና ደም ሳይካፈል ባይወለድ ኖሮ ይህ የምህረት ቃል ኪዳን በእኛና በክርስቶስ መካከል ባልተፈጸመ ነበር፡፡ እናም አጥርቶ ለመረደት የሚፈለግ ቅድስት እናቱን ኪዳነ ምህረት የማለታችን ዋናው ምክንያት ሰውነቷን የምህረት ቃል ኪዳን ታቦት በማደረግ ከርሷ በነሣው ሥጋ ዓለሙ መዳኑ ነው።