Sunday, June 11, 2017

የነፍስ ወግ (በእንተ ደናግላን)


እንደ ጢሞቴዎስ ከልጅነት ጀምሮ ከቅዱሳን መጻሕፍትና ከመንፈስ ቅዱስ እንዲሁም ከትርምት ሕይወት ስለእግዚአብሔር የተማረ፤ የልቡናውን ደጅ በመዝጋት ከሕግ መምህር ትምህርቱን የቀዳ ክርስቲያን ለእርሱ ከትዳር ሕይወት ይልቅ የድንግልና ሕይወት እንዴት የተመረጠ ሕይወት አይሆነው? ይህ ሰው ማዕረጉ ከመላእክት ወገን ነውና የሥጋ ፍትወት የራቀለት በትንሣኤ ሕይወት የሚኖር እግዚአብሔር ሳይመርጥ ኃጥኡንም ጻድቁንም እንዲወድ ሁሉን የሚወድ በአንዲት ብላቴና ፍቅር ታሥሮ እርሱዋን አስቀድሞ ሌላውን አስከትሎ መውደድ የማይቻለው፣ እንደ አምላኩ ሁሉን አስተካክሎ የሚወድ በትዳር ውስጥ ያሉቱ ጥንዶች በትንሣኤ የሚያገኙት ሙሉዕ የሆነ ፍቅር አግኝቶ የሚኖር ሰው ነው፡፡

Thursday, June 8, 2017

የነፍስ ወግ ሦስተኛ ክፍል በእንተ ትዳር

ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
02/10/2009
ትዳር መልካም ነው፡፡ የትዳርን ትርጉም ከዚህ በፊት እንደጻፍኹላችሁ በገዛ ሰውነታችን ውስጥ በምሳሌነት እናገኘዋለን፡፡  ይህ ደግሞ የሚደንቅ ነው፡፡ ይህንንም በልጆቻችን እንመለከተዋለን፡፡ እነርሱ የአንድነታችን ውጤቶች ናቸው፡፡ ቢሆንም ከዚህ በፊት በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፊ ትንታኔ የሰጠሁ ስለመሰለኝ ለዛሬ በዚህ ላይ ብዙ አልልም፡፡ ልብ እንድትሉ የምፈልገው ነገር ግን በነፍስና በሥጋ መካከል ያለው ተዋሕዶ የትዳር አምሳያ መሆኑን ነው፡፡ እረ እንደውም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቃል ከሥጋና ነፍስ ጋር በማኅፀን በተዋሕዶ አንድ መሆኑ የትዳር አምሳል እንደሆነ ያስተምረናል፡፡ እናም ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው ገና በጽንሰት ጊዜ መለኮትና ሥጋ አንድ በሆኑበት ቅጽበት ነበር፡፡ ስለዚህም በዚህ የሥጋው መጋረጃ በኩል ወደ ቅድስት መግባትን አግኝተናል:: እርሱም ከእናቱ ከቅድሰት ድንግል ማርያም የነሣው ሥጋ ነው፡፡ ይህ ሰውነቱ የገነት አምሳያ ስለሆነ ቅዱስ ኤፍሬም በተወጋው ጎኑ በኩል ወደ ገነት መግባትን አገኘን ብሎ ያስተምራል፡፡ በእርግጥም ከጎኑ በፈሰሰው ውኃ ነጽተን ከጎኑ በፈሰሰው ደም ተዋጅተን በእኛ ችሎታ ሳይሆን በእርሱ ቸርነት የክርስቶስ የአካል ሕዋሳት ለመሆን በቅተናል፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን በሆነችው ሰውነቱ በኩል መዳናችን ተፈጸመ፡፡ ሁሉ የእርሱ ከእርሱ ለእርሱ በእርሱ የሆነው ይህ ምስጢር እንዴት ድንቅ ነው!!