Tuesday, August 7, 2012

የቅድስት ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግልና



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
2/12/2004
(1996 ዓ.ም ለሰንበት ትምህርት ቤት ማስተማሪያ የተዘጋጀ)
መጽሐፍ ቅዱስና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን አባቶች ቅድስት ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግል እንደሆነች አስረግጠው ይስተምራሉ፡፡ እርሱዋ ቅድመ ወሊድ፣ ጊዜ ወሊድ፣ ድኅረ ወሊድ ድንግል ናት ፤ ሃሳቡዋም ሰውነቱዋን ለእግዚአብሔር አምላኩዋ ቀድሳ በድንግል መኖር ነበር፡፡ ይህን ከንግግሩዋ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለቅድስት ድንግል ማርያም “ ደስ ይበልሽ ጸጋን የሞላብሽ ሆይ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፡፡… ማርያም ሆይ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋን አግኝተሻልና አትፍሪ እነሆ ትጸንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ…” ባላት ጊዜ የሷ መልስ “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል” ነበር፡፡/ሉቃ. 1፥27-36/ ይህም በድንግልና ለመኖር እንደ ቆረጠች ያስረዳናል፡፡ አግብታ ልጅ የመውለድ ፈቃዱ ቢኖራት ኖሮ መልአኩን ከማን? ብላ በጠየቀችው ነበር፡፡ በተጨማሪም ወንድ ስለማላውቅ ማለቷ ወደፊትም ወንድ ባለማወቅ በድንግልና ለመኖር ለእግዚአብሔር ስለተሳልኩ እንዴት ይሆናል? ማለቷ ነበር፡፡

ቅዱስ ገብርኤልም የእርሷ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን መውለድ በተፈጥሮዋዊ ልማድ ሳይሆን፣ ያለወንድ ዘር በመንፈስ ቅዱስ ግብር እንደሆነና እናትም ድንግልም ሆና እንደምትቀጥል ከነገራት በኋላ ድንግል በመስማማቷ የእግዚአብሔርን ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን በኅቱም ድንግልና ፀንሳ ወለደችው፡፡ ወደፊትም እምወድንግል በመባል ትኖራለች፡፡
ነገር ግን ቀደም ብሎ በእግዚአብሔር የተነገረው ቃል “በአንተና /በሰይጣን/ በሴቲቱ /በድንግል ማርያም በቤተ ክርስቲያን/ መካከል በዘርህና በዘሯ መካከል ጠላትነትን አደርጋለው” የሚለው ቃል /ዘፍ.3፥15/ ይፈጸም ዘንድ በተለይ ከሁለተኛው እስከ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ውስጥ በድንግል ማርያም ዘለለማዊ ድንግልና ላይ የተለያዩ መናፍቃን ተነሥተው ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህል ቱርቱሊያን /160-220/ ሄልፊደስ /ሄልቪደስ/ /383/ ጆቬንያን /390/ ይገኙበታል፡፡ እነዚህም ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግል አትባል ልጆችንም ወልዳለች እያሉ ያስተማሩ ናቸው ፡፡ በአሁኑ ጊዜም የተነሡ አንዳንድ የፕሮቴስታንት እምነት አራማጆች ጥንት በሐሰተኛ ትምህርታቸው ቤተክርስቲያንን ያውኳት የነበሩትን ከሃዲያን ፈለግ በመከተል ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግል አትባልም ፣ ልጆችንም ወልዳለች እያሉ ያስተምራሉ፡፡ ለእነርሱ የተሳሳተ አስተምህሮ ቅዱስ ጆሮም ለሄልፊደስ የተሰጠውን ምላሽ መሠረት በማድረግ መልስ እንሰጥበታለን፡፡
የሄልፊደስ የመከራከርያ ነጥቦች
ሄልፊደስ ተርቱልያ ስለድንግል ማርያም ያስተማረውን የምንፍቅና ትምህርት ዋቢ በማድረግ ቅድስት ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግል አትባልም በማለት 383 ዓ.ም በራሪ ወረቀትን በማዘጋጀት ትምህርቱን ለማሠራጨት የሞከረ ግለሰብ ነበር፡፡ ነገር ግን በጊዜው የነበረው ቅዱስ ጀሮም ሄልፊደስ ላነሣው የመከራከሪያ ነጥቦች ሁሉ ከበቂ በላይ መልስ ሰጥቶታል፡፡ እኛም የጆሮምንና የሌሎች ቅዱሳን አባቶችን ስለ ድንግል ማርያም ዘላለማዊ ድንግልና የሰጡትን ትምህርት መሠረት በማድረግ መልስ እንሰጣለን ፡፡
የመከራከሪያ ነጥቦች
1.      በማቴ 1፥18 ላይ የተጻፈው ኃይለ ቃል ማለትም “እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች” የሚለውን ኃይለ ቃል መሠረት በማድረግ እጮኛ የሚለው ቃል የሚመለከተው ስለ እሷ መታጨት ብቻ ሳይሆን አንድ ቀን በጋብቻ አንድ እንደሚሆኑ ነው ፡፡ ስለዚህም ድንግል ማርያም ዮሴፍን አግብታዋለች ስለዚህም ልጆችን ወልዳለች ብሎ ይከራከራል፡፡
2.     ከላይ በተጠቀሰው ጥቅስ ውስጥ “ሳይገናኙ” የሚለው ኅይለ ቃልን /በእንግሊዝኛ Before They Came together/ ይዞ ጌታን ከወለደች በኋላ በግብር ያልተዋወቁ ቢሆኑ ኖሮ ወንጌላዊው እንዲህ ብሎ ባልጻፈ ነበር ስለዚህም ጌታን ከወለደች በኋላ በግብር አውቋታል ይላል፡፡
3.     በእንግሊዘኛው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ /Fear not to take your wife/ ሚስትህን ለመውሰድ አትፍራ የሚለውን ኃይለ ቃል ይዞ ሚስት እንድትሆነው ዮሴፍ እንደተሰጠች ፣ እንዲህም ስለሆነ ድንግል ሆና ስለመኖሯ ምንም ማረጋገጫ አለመኖሩ /ማቴ.1፥24/ ማስረጃ ነው ይላል፡፡
4.    “የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም” /ማቴ.1፥25/ የሚለው ኃይለ ቃልን መሠረት በማድረግ በኩር የሚለው ቃል ተከታይ እንዳሉት የሚጠቁም ነው ፡፡ በኩር ማለት ከታናናሾች ታላቅ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሌሎች ልጆች ወልዳለች በማለት ይከራከራል ፡፡
5.     ወንጌላዊው “እስክትወልድ” ድረስ ማለቱ ከወለደች በኋላ በግብር እንደተዋወቁ የሚጠቁም ነው/ማቴ.1፥25 ይላል፡፡
6.    “አላወቃትም” የሚለው ቃል በራሱ የሚጠቁመው በግብር መተዋወቃቸው ነው /ማቴ.1፥15/ ብሎም ይፈታዋል፡፡
7.     መጽሐፍ ቅዱስ ጌታ ወንድሞች እንዳሉት ያስረዳልና ይህም ሌሎች ልጆችን ስለመውለዱዋ በቂ መረጃ ነው ብሎ ይከራከራል፡፡ /ማቴ.12፥46፣ ዮሐ.2፥12፣ 7፥3-5፣ ዮሐ.1፥14፣ ገላ.1፥19፣  2፥8፣ 1ኛ ቆሮ.9፥4-5/
ለሄልፊደስ የተሰጡ መልሶች
1.    እጮኛ
በመጽሐፍ ቅዱስ ድንግል ማርያም ለዮሴፍ እንደታጨች ይናገራል ነገር ግን ሄልፊደስና ሌሎችም መናፍቃን እንደሚያስቡት ሳይሆን ከእነርሱ አስተሳሰብ ፈጽሞ የተለየ ነው፡፡ ምክንያቶችም አሉት ምክንያቶቹን እንደሚከተለው ቀርበዋል ፡፡

1.1.           ድንግል ማርያም ኃይለ አርያማዊት ወይም ከሰው ወገን አይደለችም ብለው አንዳንዳንድ የስህተት ትምህርት አራማጆች እንደሚነሡ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ የእነዚህን የመናፍቃንን አፍ ለማዘጋትና ሰው እንደሆነች ለማመልከት እርሱ ባወቀ ለዮሴፍ እንድትታጭ አድርጓታል፡፡ ይህንን ቅዱስ አትናቴዎስ እንዲህ በማለት ያብራራዋል፡፡ “And this Isaiah pointed to in his prophecy in the word  behold the virgin (Is 7:14) while st. Gabrial is sent to her not simply to virgin but to virgin betrothed to a man, in order that by means of bretrothed man he might show that may was really a human being” ሲተረጎም “ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች” ማለቱና ወንጌላዊውም ስለቅዱስ ገብርኤል ወደ ድንግል መላክ ሲያስተምር “ከዮሴፍ ወደታጨች ከአንዲት ድንግል ተላከ” ማለቱ “እጮኛ” በሚለው ቃል እርሱዋ ፍጹም ሰው መሆኑዋን ለማሳየት ነው” ብሏል፡፡ በዚህም ምክንያት ቅድስት ድንግል ማርያም ከሰዎች ወገን ስለመሆኑዋ ለማስገንዘብ ሲባል እግዚአብሔር ባወቀ ለዮሴፍ ታጨች ፡፡  
1.2.          በመንፈስ ቅዱስ ግብር ጌታን በመፀነሷ ምክንያት ከአይሁድ አላዋቂነት የተነሣ ከሚመጣባት ከድንጋይ ውግረት ለመጠበቅ ዘዳ.22፥20-21
1.3.          በአይሁድ የዘር ሐረግ የሚቆጠረው በወንድ በኩል ስለሆነ በዮሴፍ አመካኝቶ /አስጠግቶ ወንጌላዊው የድንግልን የዘር ሐረግ ለመናገር ስለፈለገ ነው፡፡
1.4.          ዮሴፍ ድንግል ማርያም ወደ ግብጽ በተሰደደች ጊዜ ጠባቂና አገልጋይ እንዲሆናት ሲባል ለዮሴፍ እንድትታጭ ሆናለች ፡፡
በእነዚህ ምክንያቶች የተነሣ እግዚአብሔር ባወቀ ሄልፊደስና ግብረ አበሮቹ እንደሚሉት ሳይሆን ድንግል ማርያም ለዘመዷ ዮሴፍ እንድትታጭ ሆናለች፡፡
2.   ሳይገናኙ /Before they came together/
ሄልፊደስ “ሳይገናኙ” የሚለውን ቃል ይዞ ጌታን ከወለደች በኋላ ቃሉ እንደሚመሰክረው በግብር አውቋታል ብሎ ይከራከራል፡፡ ይህ ግን ፈጽሞ ስሕተት ነው፡፡ ወንጌላዊው እንዲህ ለማለት የፈለገው ጌታን የፀነሰችበትን ጊዜ ለመጠቆምና ከዚያም በኋላ ጋብቻ እንዳልተመሠረተ ለማስረዳት ነው፡፡ ቅዱስ ጀሮም ለዚህ መልስ ሲሰጥ በምሳሌ እንዲህ ብሏል፡፡ “Helvedius, Before he repent, was cut off by death” “ሄልፊደስ ንስሐ ከመግባቱ በፊት በሞት ተወግዷል፡፡” ብንል ይህ ማለት “ከሞተ በኋላ ንስሐ ገብቶአል” ማለት ነውን ? አይደለም ነገር ግን ንስሐ ጨርሶ እንዳልገባ የሚያስረዳ ነው ፡፡ እንዲሁ ወንጌላዊው ሳይገናኙ (before they came together) ማለቱ ትጭጭቱ ወደ ጋብቻ እንዳልተቀየረ በተቃራኒው ግን ድንግል ማርያም በእናትነት ዮሴፍ ደግሞ በጠባቂነትና በአገልጋይነት በባል ሽፋን አብረው መኖራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡  
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር “ወንጌላዊው “ሳይገናኙ” ማለቱ ወደ ሙሽራው ቤት /ጫጉላ ቤት/ ሳትወሰድ በፊት ማለቱ አይደለም፡፡ በእርግጥ ጌታን ከፀነሰች በኋላ ቅድስት ድንግል ማርያም ከዮሴፍ ቤት ኖራለች ፡፡ ይህ ደግሞ አግብታዋለች ማለት ግን አይደለም፡፡ ምክንያቱም የድሮ ሰዎች የታጨችላቸውን ድንግል በቤታቸው የመጠበቅ ልምድ ነበራቸውና ነው፡፡ /ዘፍ.19፥8-14/ የሎጥ አማቶች ከሎጥ ሴት ደናግላን ልጆች ጋር በአንድ ቤት እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል” ብሏል፡፡  ይህም ድንግል ማርያም ከዮሴፍ ጋር አብራ ኖራለች መባሉ ሌላ ትርጉም የሚያሰጥ አይደለም፡፡
3.   ሚስት
በእኛ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሚስት የሚለው ቃል ተጽፎ አናገኝም፡፡ ነገር ግን በግሪኩ እና በእንግሊዘኛው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ድንግል ማርያም የዮሴፍ ሚስት እርሱም ባል ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ወደ አማርኛ በተተረጎመ ጊዜ ግን እጮኛ ተብሎ ነው የተተረጎመው በዚህ ጉዳይ ላይ እኛ አንቸገርም ነገር ግን ለግንዛቤ ያህል ማወቁ ስለሚጠቅመን በመጠኑ ለመመልከት እንሞክራለን፡፡ በመጀመሪያ ሄልፊደስ ለመከራከሪያ የተጠቀመባቸውን ጥቅሶች እንመልከት፡፡ “Fear not to take Mary your wife….. “Joseph arose from his sleep, and did as the angel of the Lord commanded him and took unto him his wife” ይህም “ሚስትህ ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ… “ዮሴፍ ከእንቅልፉ ነቅቶ የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ ሚስቱ ማርያምንም ወሰደ” /ማቴ.1፥20-24/ የሚል ትርጉምን ይሰጠናል ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ይህን ጠቅሶ የሚከራከር ከተገኘ በዕብራውያን ልማድ የታጨችን ድንግል ሚስት ብሎ መጥራት ልማድ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል ፡፡
ለምሳሌ በዘዳግም 22፥24 ላይ “ማናቸውም ሰው ድንግልና ያላትን ልጃገረድ ቢያጭ ሌላ ሰውም በከተማው ውስጥ አግኝቶ ከእርሷ ጋር ቢተኛ ሁለቱንም ወደዚያች ከተማ በር አውጡአቸው ብላቴናይቱ በከተማ ውስጥ ሳለች አልጮኸችምና ሰውየውም የባልንጃራውን ሚስት አስነውሯልና እስኪሞቱ ድረስ በድንጋይ ውገሯቸው፡፡” ይላል ፡፡  በዚህ ኃይለ ቃል ውስጥ የታጨች ድንግል ሚስት ተብላ እንደተጠራች እናስተውላለን፡፡ በተጨማሪም /ዘዳ.20፥7/ን መመልከት ነገሩን ግልጽ ያደርግልናል፡፡ በዚህ ምክንያት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም ወንጌላዊውም ለዮሴፍ የታጨችውን ድንግል ማርያምን ሚስት ብለዋታል ቢባል እንኳ ድንግል አይደለችም ለማለት አስበው ሳይሆን የመጽሐፍና የሕዝቡን ልማድ መሠረት አድርገው ሲናገሩ ነው ብለን መረዳት እንችላለን ፡፡
ቅዱስ ጀሮም ዮሴፍ የድንግል ማርያም ባል እርሱም ሚስት ተብለው የመጠራታቸውን ምክንያት ሲያብራራ እንዲህ ይላልከዮሴፍ ከኤልሳቤጥና ከራሷ ከድንግል ማርያም እንዲሁም ከሌሎች ጥቂት ቅዱሳን በቀር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዮሴፍ ልጅ እንደሆነ ብዙዎች ወይም ማኅበረሰቡ ያምን ነበር፡፡ ወንጌላውያኑም ምንም እውነታውን ቢያውቁ በብዙኃኑ የሚታመንበትን አስተሳሰብ በመጽሐፍ ቅዱስ አስፍረውልን እናገኛለን ፡፡ በእርግጥም በዘመኑ የነበረው ማኅበረሰብ ስለድንግል ማርያም እንዲህ ዐይነት አመለካከት ነበረው ብሎ ለማስገንዘብ ወንጌላውያኑ መጻፋቸው ተገቢ ነበር ፡፡ ይህ የአንድ ትክክለኛ የታሪክ ጸሐፊ ጠባይ ነው፡፡  ለምሳሌ ያህል በሉቃስ 227 ላይ እንዲህ የሚል ቃል ተጽፎ እናገኛለንወላጆቹም እንደ ሕጉ ልማድ ያደርጉለት ዘንድ ሕፃኑን ኢየሱስን በአስገቡት ጊዜ እርሱ ደግሞ ተቀብሎ አቀረበው” ይላል፡፡ በዚህ ኃይለ ቃል ውስጥ ወንጌላዊው ክርስቶስ የዮሴፍ ልጅ አለመሆኑ ጠፍቶት አይደለም ዮሴፍን ወላጅ ብሎ የጠራው ፤ ነገር ግን ብዙኀኑ እንዲህ ብለው ያምኑ ነበር ለማለት ነው ፡፡ ለበለጠ መረጃ ሉቃ.21-43 መመልከት ይጠቅማል፡፡
በሌላ ቦታ ደግሞ ድንግል ማርያም ራሷ ኢየሱስ ክርስቶስ የዮሴፍ ልጅ አለመሆኑን እያወቀች ዮሴፍን የክርስቶስ አባት እንዳለችው እንመለከታለንልጄ ሆይ ለምን እንዲህ አደረግህብን እነሆ አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበር” /ሉቃ.248/ እንዲል፡፡ ይህ የሚያሳየው ቅድስት ድንግል ማርያምን አስመልክቶ ኅብረተሰቡ የጠራ ግንዛቤ እንደሌለው የሚያስረዳን ነው ፡፡ በእርግጥም እግዚአብሔር አምላክ ከማኅበረሰቡ መንፈሳዊ ብስለት ጉድለት የተነሣ ለጊዜውም ቢሆን የእርሱ በኅቱም ድንግልና መወለድ ተሰውሮ እንዲቆይ ሲል ዮሴፍ ከቅድስት ድንግል ማርያም እንዳይለይ “የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ ከእርስዋ የሚወለደው በመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ”(ማቴ.2፡20) በማለት መከልከሉን እናስተውላለን ፡፡ በዚህም ምክንያት አይሁድ ዮሴፍን እንደ ክርስቶስ አባት ድንግልን ደግሞ እንደ ዮሴፍ ሚስት አድርገው ይቆጥሩ ነበር፡፡ እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዮሴፍ ልጅ እንዳልሆነ ሁሉ ድንግል ማርያምም የዮሴፍ ሚስት አይደለችም የጌታ ወንድሞች የተባሉትም የእርሱ የሥጋ ወንድሞች አይደሉም፡፡ ነገር ግን ዮሴፍ በባለቤት ስም መጠራቱ ድንግል ማርያም ከሚመጣባት ከአይሁድ ጥቃትና በስደቷ ጊዜ ረዳት እንዲሆናት እግዚአብሔር አቅዶ ያደረገው መሆኑን መገንዘብ እንችላለን” ብሏል ፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም እውነተኛ ሚስቱ ናት ለሚሉ ሰዎች  “for if he had known her, and had kept her in the place of a wife, how it that our Lord commits her as unprotected, and having no one, to his disciple, and commands him to take her to his own home?” “ዮሴፍ ቅድስት ድንግል ማርያምን በግብር ያወቃትና ሚስቱ ያደረጋት ቢሆን ኖሮ እንዴት ጌታችን እርሱዋን አንድም ጠባቂና ረዳት እንደሌላት ሰው ቆጥሮ  ለደቀመዝሙሩ ለዮሐንስ ይሰጣታል ? እርሷንስ በቤቱ እንዲጠብቃት ለምን ያዘዋል ?” ብሎ ይጠይቃቸዋል፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ድንግል ማርያምን የዮሴፍ ሚስት ወይም እጮኛ ቢላትም ዋናው ቁምነገር ዮሴፍ ለእርሷ ጠባቂዋ አገልጋይዋ እንደሆነ ለመናገርና ከፈተናዎች ሁሉ እርሷን ለመታደግ እንዲሁም እግዚአብሔር ባወቀ በኅቱም ድንግልና ጌታን ስለመውለዱዋ ጻድቅ የሆነው ዮሴፍ እውነተኛ ምስክር እንዲሆን በማሰብ ነው፡፡
ይቀጥላል.......

7 comments:

  1. bewent edih ayinet timihirit neber yetemanew edhi telatina kehadianin beeritu timihite masafer wenidima tsegawin yabizalih dinigil titebikihi!!!!!!!!!!!

    ReplyDelete
  2. kale hiwot yasemalen

    ReplyDelete
  3. Kale heyweten yasemalen bewenet betam melkamen asetemare yehune temerte new beze agatame salaswekhe ye malalfew aned neger ale esum ke ena gar hunew tehufehen ye meyanbu ke 12 yalansu lejoche alu ensum bewenet be egzyabher sem meseganachewen akerbwal tegawen yabzalhe

    ReplyDelete
  4. እግዚአብሔር ይስጥልኝ ወገኖቼ አምላክ እርሱን ወደማወቅና በእርሱ ዘለዓለማዊነት ውስጥ ፍቅሩን እየተመገብን እንድንኖር ያብቃን፡፡ በጸሎታችሁ ደግሞ አስቡኝ፡፡

    ReplyDelete
  5. እግዚአብሔር አምላክ ማደሪያው ሁሉ ንጹሕና ቅዱስ ፍጹምም ነው።ስለሆነም እርሱ ያደረበት
    ሰውም ሆነ ቦታ ወይንም ንዋይ ሁሉ ቅዱስ ይባላል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም
    የአምላክ ማደሪያ ሆና ስለተገኘች ቅድስት ትባላለች ። የተገኘችውም እግዚአብሔር
    ካደረባቸው ቅዱሳን ስለሆነም ጭምር ቅድስት ተብላለች።ነብዩ ዳዊትም “ልዑል ማሪያውን ቀደሰ” መዝ. ፵፭፥፬-፭ በማለት አስቀድሞ
    በፈጣሪ ዘንድ የተቀደሰች መሆኗን ይናገራል። መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም “ከሴቶች ተለይተሽ
    የተባረክሽ ነሽ የማኅጸንሽም ፍሬ የተባረከ ነው” ሉቃ. ፩፥፳፰ በማለት ቅድስናዋን መስክሯል።ነብዩ ሕዝቅኤል በምዕራፍ ፵፬፥፪ ላይ “እግዚአብሔር ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ
    አይከፈትም ሰውም አይገባበትም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ
    ይኖራል” ይላል። ይህ ቃል የተነገረው ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ነው ሰው
    የሆነው አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በገባበት በዚያ በር ማንም አልገባም ማንም አልወጣም።የበኲር ልጇን እስክትወልድ አላወቃትም ተብሎ ቢነገርም ማቴ. ፩፥፳፭ በኲር ሁል ጊዜ
    ተከታይ አለው ማለት እንዳልሆነ ይህ የነብዩ የሕዝቅኤል ትንቢት ያረጋግጣል፤ ነብዩ
    ኢሳይያስ በትንቢቱ ኢሳ.፯፥፲፬ ላይ “እነሆ ድንግል ትጸንሳለቸ ወንድ ልጅም ትወልዳለች”
    ይላል፤ ቅዱስ ሉቃስ በወንጌል እንደጻፈው የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል የጌታን ከእርሷ
    መወለድ ሊያበስራት በተላከ ጊዜ “ወደ አንዲት ድንግል ተላከ የድንግሊቱም ስም ማርያም
    ነበረ ይላል”፤ ሉቃ.፩፥፳፮ በተጨማሪም በመኃልይ ፬፥፲፪-፲፭፤ ሉቃ.፩፥፴፬ ላይ
    ስለድንግልናዋ ተጽፎ ይገኛል።ለዚህም ነው እመቤታችንን ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ እያልን ዘወትር
    የምናመሰግናት፤ የተመሰከረላት ፍጹም ድንግል ናትና፤ ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስን ከመጽነሷ
    በፊት፣ በጸነሰች ጊዜ፣ ከጸነሰችም በኋላ፣ ከመውለዷ በፊት፣ በወለደች ጊዜ፣ ከወለደችም
    በኋላ፣ ፍጹም ድንግል ናት። ሌሎች ሴቶች ከወለዱ በኋላ እናት እንጂ ድንግል አይባሉም፤
    እርሷ ግን እናትም ድንግልም ናት።

    ReplyDelete