በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
22/09/2009
እናንተዬ እኔ ረቂቋ ነፍስ ይህን ሁሉ ሳስብ ሐዲስ ኪዳንን ዘንግቼ ብሉይ ኪዳን ውስጥ ያለሁ መሰለኝ፡፡ ለመሆኑ በክርስቶስ ያለኝ ተስፋ ወዴት ሄደ? በርሱስ ያገኘሁት ሕይወት የት ደረሰ?? ክርስቶስን ሳስብ ሚስቴ የሆነችው የሥጋዬ በደል ፈጽሞ ይጠፋል ቀንበሯም ቀሊል ይሆንልኛል፡፡ እንደውም እርሷ ባትኖር ኖሮ እኔ ነፍስ እድን ነበርን? ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ እረ በፍጹም ሥጋዬ ባትኖር ኖሮ ከአምላክ የመለየትን ትርጉም በምን እረዳው ነበር? ለንስሐስ እንዴት እተጋ ነበረ? እንዴትስ አምላኬን አየው ነበረ? እኔ ብቻ ሳልሆን መላአክትስ ቢሆን ከነርሱ በእጅጉ የሚረቀውን አምላክ ለመመልከት የበቁት በማን ሆነና?
ጥንቱን ከመላእክት መፈጠር በፊት እርሱ የሁሉ ገዢ የሆነው ፈጣሪዬ አምሳያው የሰው ነበር፡፡ በእርሱ አምሳያ እኔን በተለይ ግን ሥጋዬን ፈጠራት፡፡ እንዲህ ማለቴ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ እኔ በእርግጥ በመላእክት ዘንድ እታያለሁ በአምላኬ ዘንድም የተገለጥሁ ነኝ፡፡ ቢሆንም እኔም ሆንኹ ሰማያውያን መላእክት በላይ በአርያም አምልኮአችንን የምንፈጸመው በሰው አምሳል ተገልጦልን ነበር አሁንም ወደፊትም የሚሆነው ይህ ነው፡፡ ስለዚህ ነቢዩ ሕዝቅኤል፣ ኢሳይያስና ዮሐንስ ወንጌላዊው በኪሩቤል ጀርባ ላይ በሰው አምሳል ተቀምጦ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ተብሎ ሲመሰገን ተመለከቱ፡፡: ዳንኤልም “ዙፋኖችም እስኪዘረጉ ድረስ አየሁ፥ በዘመናት የሸመገለውም ተቀመጠ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ፥ የራሱም ጠጕር እንደ ጥሩ ጥጥ ነበረ ዙፋኑም የእሳት ነበልባል ነበረ፥ መንኰራኵሮቹም የሚነድድ እሳት ነበሩ፡፡”(ዳን.7፡9) ብሎ ያየውን ጻፈልን።
ይህ ብቻ ግን አይደለም መዳኔ የተፈጸመው በሥጋዬ ነው፡፡ መራብ መጠማት የማን ባሕርይ ነው? መከራ መቀበልስ የማን ባሕርይ ነው? መድማት መቁሰል መታመምስ የማን ባሕርይ ነው? መሞትስ የማን ባሕርይ ነው? የሥጋ አይደለምን? እነዚህ ባሕርያት ለሥጋ እንጂ ለእኔ ባሕርይ የሚስማሙ አይደሉም፡፡ እኔ በባሕርዬ መራብ መጠማት የለብኝም መራብ መጠማቴ ከአምላኬ ቃል፣ ጸጋ፣ እንዲሁም መንፈሳዊ ሕይወት መራቄ ነው፡፡ መድማት መቁሰል መታመም በእኔ ባሕርይ ውስጥ የሉም መሞትም እንዲሁ፡፡ የእኔ መሞት ጌታ እንዳለው ከእርሱ መለየት ለምድራዊ ነገር ሙሉ ጊዜ ሰጥቶ መትጋት ነው፡፡ ስለዚህ ጌታችን ለሙታን ወንጌልን ልሰበክ መጣሁ፣ ሙታን ሙታናቸውን ይቀብሩ ዘንድ ተዋቸው፣ እኔ የአብርሃም አምላክ የይሰሐቅ አምላክ የያዕቆብ አምላክ ነኝ እኔ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለሁም አለ፡፡ ይህ ሞት ግን መቃብር የሚጥል ሞት አይደለም፥ ከአምላክ ረድኤትና ልጅነት የሚያርቅ ሞት እንጂ፡፡
ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን ከዚህ ክፉ ሞት ያዳነኝ። በሥጋ ተርቦ ተጠምቶ፣ የርኩሳን ምራቅ ጢቅ ተደርጎበት፣ ተፊዞበት፣ ተቀልዶበት፣ ሥጋው አልቆ አጥንቱ እስኪታይ ድረስ በጅራፍ ተገርፎ፣ ደሙ እንደ ጅረት ፈስሶ፣ ጽኑ ጭካኔ ተፈጽሞበት፣ መስቀል ላይ ተቸንክሮ፣ በጦር ጎኑ ተወግቶ በሥጋ ሞቶ አዳነኝ፡፡ ይህንን ባሰብኹ ጊዜ ሁሉ እንባዬ ኩልል ብሎ በጉንጮቼ ላይ ይፈሳል። አዝናለሁ እተክዛለሁ፡፡ የእኛን የኃጢአታችንን ከብደትና እርሱ ለእኛ ያለውን የማይመጠን ፍቅሩን በዚህ ሕማሙ ውስጥ እመለከታለሁ፡፡
መላእክት ከዚህ ቀደም በአምሳያው ይመለከቱት የነበሩትን ፈጣሪያቸውን ሰው ሆኖ በእናቱ እቅፍ ውስጥ ሲያገኙት አድንቀው ስብሐት ለአግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ ብለው ደስታቸውን ገልጠው ነበር፡፡ ስለእኛ ያን ጽኑ መከራ በአሕዛብ ወታደሮች ሲፈጸምበት ሲመለከቱስ ምን ብለው ይሆን ? ያ ጽኑ የሆነ ጭካኔ በክብር ጌታ ላይ ተፈጽሞ እርቃኑን ሲሰቀል ጸሐይ ብርሃኗን ከለከለች፣ ጨረቃም ደም መሰለች ከዋክብት ረገፉ ፡፡ እናንት በአንድ የጠፋ በግ የምታዝኑ በመመለሱ እጅግ ደስታን የምታደርጉ ብሩካን የእግዚአብሔር ሠራዊት የሆናችሁ ቅዱሳን መላእክት ሆይ ይህን ጽኑ የሆነውን የጌታን መከራ ስትመለከቱ ሃዘናችሁ እንዴት ነበር? እኔ ነፍስ ይህን ለመረዳት አሰላሰልሁ አሰላሰልሁ ግን መረዳት ተሳነኝ፡፡ ቢሆንም ግን ምንም እንኳ ሥጋዬ በምድር አምላኬን እንዳላስብ ከባድ ቀንበር ሆናብኝ የነበረች ብትሆንም ጌታ በእርሷ ባሕርይ ተገኘቶ አድኖኛልና እርሷን ዘወትር ኑሪለኝ ብዬ አመሰግናታለሁ፡፡ የቀድመውንም በደሏን ማሰብ አቁሜአለሁ፡፡
እርሱ አምላኬ የእኔንም የሥጋንም ባሕርይ ተካፍሎ ሰው ሆኖ ይመላለስ እንጂ መዳኔን የፈጸመልኝ በሥጋዬ በኩል ነው፡፡ እርሱ ነፍሱን ከሥጋው ለይቶ ከጎኑ በፈሰሰው ውኃ አጥምቆ ሥጋዬንም እኔንም ከኃጢአታችን አጠራን፤ በደሙም ዋጅቶ የራሱ አደረገን፡፡ እነዚህ ግን የሥጋ ገንዘቦች ናቸው፡፡ እኔ የተለየሁበት መለኮት ግን የተዋሐደውን ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ እርሱ በእኔ እኔም በርሱ እንድኖር አበቃኝ፡፡ እንዲያ ለጉስቁልና የዳረገችኝን ሥጋዬን ጌታ ለመዳኔም ምክንያት አደረጋት፡፡ በእርሷ ፍላጎት ምክንያት በምድር ላይ ብቆሰቁልም በእርሷ ባሕርይ ምክንያት መዳኔ ስለተፈጸመ በደሏን ዳግም አላስብም፡፡ ቢሆንም ግን አርአያ የለኝምና ወደ ቀድሞ በደሌ እመለሳለሁ ብትል ለሥጋ ምክንያት የላትምና ወዮላት፡፡ አሁን ሥጋዬ እንዴት መኖር እንዳለባት ከአምላኳ ተምራለች፡፡ ከእንግዲህ የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንጂ የአጋንንት ማደሪያ ዋሻ አይደለችም፡፡ እኔም ክብር ይግባውና መንፈስ ቅዱስ በሚሰጠኝ ማስተዋል ለሥጋዬ እንደ ካህን በመሆን ከርኩሰት ሁሉ እጠበቃት ዘንድ ይገባኛል፡፡ ይህ ደግሞ ለእኔ ደስታዬ ነው፡፡ አምላኬ ሆይ በጽድቅ ሥራ የጨከንኹ እሆን ዘንድ ሁሌም ቢሆን ሕማምህን ማሰብ ስጠኝ፡፡
አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ደርሶ ለወደደንና የልጅነትን መንፈስ ለሰጠን ለእግዚአብሔር አብ፣ ነፍሱን እስከመስጠት ደርሶ እኛኝ ለወደደን ለልጁ ለእግዚአብሔር ወልድ፣ ከጽንሰቱ እስከ ትንሣኤው ከእርሱ ላልተለየ በእኛ ላይ በማደር ለእኛ የእርሱ የሆነውን ልዩ ልዩ ጸጋዎችን ለሰጠን፥ ለሚያጽናናንና ለሚያስተምረን ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ክብር ምስጋና ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
Thank you my brother for your comment. But I amazing you that you read Amharic. I saw your blog also your collection is incridable.
ReplyDelete