Monday, August 20, 2012

ደብረ ታቦር በቅዱስ ኤፍሬም(የመጨረሻ ክፍል)



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
14/12/2004
ክብር ለእርሱ ለወደደን ይሁንና ስለፍቅሩ የእኛን ሥጋ በመልበሱ ምክንያት እኛ የሰው ልጆች የክብሩን ብርሃን ለማየትና ድምፁንም ለመስማት በቃን፡፡ ስለዚህም ከእናታችን በነሣው ሰውነት በኩል ግርማ መለኮቱን  ለደቀመዛሙርቱ ባሳያቸው ጊዜ ሕሊናቸውን ስተው ወድቀው አልተጎዱም ነበር፡፡ ነገር ግን እያዩት እንቅልፍ ይዞአቸው ሄደ፡፡ በዚህም ስለምን ምክንያት በመለኮታዊው ግርማ ለእኛ እንዳልተገለጠልንና ስለምን ሥጋችንን መልበስ እንዳስፈለገው አስተማረን፡፡
ሦስቱ ዋነኞቹ ሐዋርያት የእርሱ ብርሃነ መለኮቱን ሳይሆን ግርማውን ባዩ ጊዜ እንቅልፍ የጣላቸውና ምን እንዳዩና ምን እንደሰሙ ያላስተዋሉ ከሆነ እንዲሁም ስምዖን ጴጥሮስ እንኳ የሚናገረውን ለይቶ እስከማያውቅ ድረስ ደርሶ መረዳታቸው የተወሰደ ከሆነ እንዴት እኛ የእኛን ሥጋ ሳይለብስ መለኮትን ልናይ ከእርሱ በቀጥታ ልንማር ይቻለን ነበር? እኔስ ለእኛ በመለኮታዊው ብርሃን ተገለጠልን ልል እንዴት ይቻለኝ ነበር? የእኛን ሥጋ ገንዘቡ ባያደርግ ኖሮ በምን መንገድ ራሱን ለእኛ ይገልጥልን ነበር?  በእኛው አንደበት ባይናገረን ኖሮ እንዴት ከመለኮት በቀጥታ ልንማር ይቻለን ነበር? በሚታይ አካል ለእኛ ባይገለጥልን ኖሮ እንዴት ተአምራቱን ሲፈጸም እርሱ እንደፈጸመው ተረድተን ልናምነው ይቻለን ነበር?