Friday, March 23, 2012

ነጻ ፈቃድና ቃና ዘገሊላ(ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
15/07/2004
ስለእኛ መዳን ራሱን ዝቅ በማድረግ የባሪያውን መልክ ይዞ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም በሆነ ትሕትና “በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፣ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ”(ሉቃ.7፡34)ብለው ስም እስኪሰጡት ደርሶ ራሱን ዝቅ በማድረግ ከእናቱና ከደቀመዛሙርቱ ጋር በቃና ዘገሊላ በባሪያው በዶኪማስ ሰርግ ላይ በእንግድነት ተገኘ፡፡ በዚያን ጊዜ ለሰርጉ የተጣለው ወይን ጠጅ አልቆ ነበርና ሙሽራው ሲጨነቅ አይታ እናታችን ቅድስት ንጽሕት ድንግል ማርያም ልጁዋን ወዳጁዋን “ወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” በማለት ልመናን አቀረበችለት፡፡ ጌታችንም “አንቺ ሴት ካንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም”ብሎ መለሰላት፡፡(ዮሐ.2፡3-4) ይህ የጌታችን መልስ ቅድስት እናታችን ለልጁዋ ለወደጁዋ ልመና ስለማቅረቡዋ ምስክር ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን አስመልክቶ የዮሐንስ ወንጌልን በተረጎመበት 21ኛው ድርሳኑ ለእኛ እንዲህ ብሎ ያስተምረናል፡፡