ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
29/06/2004
ይህቺ ቀን
ለቅዱሳን ነቢያት ነገሥታትና ካህናት የደስታቸው ቀን ናት፡፡ በዚህች ቀን በይሁዳ አውራጃ በቤተልሔም እንደ ተስፋ ቃሉ የሰው ልጆችን
ከኃጢአት ሊያድናቸው ከቅድስት ንጽሕት ድንግል ማርያም አማኑኤል ተወለደ፡፡ እነሆ ድንግል አስቀድሞ በነቢዩ ኢሳይያስ “እነሆ ድንግል
ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች”(ኢሳ.7፡14)ብሎ የተነገረው የትንቢት ቃል እውን ሆነ፡፡ አሕዛብን
ወደ እርሱ የሚያቀርባቸው በዚች ቀን ተወለደ፡፡ ነቢዩ ዳዊት ስለእርሱ የተናገረው ትንቢት ዛሬ ተፈጸመ፡፡(መዝ.130፡1-7) ሚክያስ
የተናገረው የትንቢት ቃልም እንዲሁ፡፡(ሚክ.5፡2) ጌታችን በኤፍራታ እረኛ የሆነው ክርስቶስ ተወለደ፡፡(ማቴ.2፡1-2) በበትሩም(በመስቀሉም) በእርሱ የታመኑትን ይጠብቃቸዋል፡፡
ከያዕቆብ ኮከብ ወጣ ከእስራኤልም ራስ የሆነው ተነሣ፡፡ በልዓም አስቀድሞ “አያለሁ አሁን ግን አይደለም እመለከታለሁ በቅርብ ግን
አይደለም ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል ከእስራኤልም በትር ይነሣል”ብሎ የተናገረው የትንቢት ቃል በዛሬዋ ቀን ተፈጸመ፡፡(ዘኁል.24፡17)
በሕቡዕ የነበረው ብርሃን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ታየ፡፡ በነቢዩ ዘካርያስ የተነገረው ብርሃን ዛሬ በቤተልሔም አበራ!(ዘካ.4፡1-3)