Sunday, January 15, 2012

“እናንተ የመንግሥቱ ካህናት ናችሁ”(1ጴጥ.2፡5-9)



ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
5/04/2004
አዲስ አበ
መቼም ካህን የሚለውን ቃል ትርጉም የሚያጣው ክርስቲያን አይኖርም፡፡ ለማስታወስ ያህል ግን ካህን ማለት አገልጋይ ማለት ነው ፡፡ በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከል ሆኖ እግዚአብሔርንም ምዕመናኑንም የሚያገለግል መካከለኛ ፡፡ ይህ ይጠፋዋል ተብሎ የሚታሰብ አንድም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን የለም ፡፡ ባይሆን ወዳጄ ሆይ ይልቁኑ አንተ ራስህ ስለእነርሱ መዳን ለሞተላቸው ነገር ግን ወደ ክርስትና እምነት ላልተመለሱ ዘመዶችህ በምግባር አብነት ሆነኻቸው፣ በቃልም አስተምረሃቸው ወደ ጥምቀት በማቅረብ ከእግዚአብሔር ጉባኤ እንዲቀላቀሉ ቤተክርስቲያን ካህን አድርጋህ እንደሾመችህ ታውቃለህን ? መቼም እንዲህ ስትባል “እንዴ ! ምነው! ቤተክርስቲያንን ይመሩና ያስተዳድሩ ዘንድ ጳጳሳት የሾሟቸው ካህናት የት ሄደው ነው እኔን ካህን ማለትህ ? ብለህ ልትጠይቀኝ ትችላለህ ፡፡
እርግጥ ነው በጳጳሳት የተሾሙ ካህናት በጥምቀት የክህነት ሥልጣንን ያገኙትን የክርስቲያኑን ማኅበረሰብ መንፈሳዊ ጤንነት በመጠበቅ የክህነት አገልግሎታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ለመርዳት በቤተክርስቲያን ውስጥና ለክርስቲያኑ ማኅበረሰብ የሚያገለግሉ ካህናት ናቸው፡፡ በነገረ መለኮት ትምህርት ይህ ክህነት ምሥጢራት የሚፈጸምበት ክህነት(sacramental priesthood) ተብሎ ይታወቃል፡፡  ነገር ግን አንድ ተዋጊ ጀነራልም(2ጢሞ.2፡3-4) ተባለ እግረኛ(ኤፌ.6፡10-17) ያው ወታደር ነው፡፡ ተግባራቸውም ለሚዋጉለት መንግሥት ወይም ንጉሥ ጠላትን ድል በመንሳት ምርኮን ማምጣት ፣ የንጉሡን ግዛት መጠበቅና ማስፋፋት እንዲህም ሰላምን ማስፈን ነው፡፡ ልዩነታቸው አንደኛው ከላይ ሆኖ ወታደሩን መምራቱ ፣ ማደራጀቱ ፣ የውጊያ ትጥቅን ማሟላቱና የወታደሩን ጤንነት መንከባከቡ ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ለወጣው ደንብና ሥርዐት ተገዝቶ የተሰጠውን ግዳጅ በአግባቡ መወጣቱ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች የሥራ ድርሻቸው የተለያየ ቢሆንም ሁለቱም ተግባራቸው ጠላትን መደምስስ ነው፡፡ እኛም ክርስቲያኖች እንዲሁ ነን ፤ ሁላችንም የክርስቶስ ወታደሮች ነን፡፡ ተግባራችንም የጽድቅን ጥሩር ለብሰን የመዳንን ቁር በራሳችን ላይ ደፍተን የቃሉን ሰይፍ ታጥቀን ጠላት ዲያብሎስን ድል በመንሳት በእርሱ አገዛዝ ሥር ወድቀው የነበሩትን ነፍሳት ለክርስቶስ መማረክና ከቅዱሳን ሕብረት መቀላቀል ነው፡፡ (ኤፌ. 6፡10-17) ስለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ” (1ጴጥ.2፡4) ብሎ ማስተማሩ፡፡ ይህኛው ደግሞ የንጉሥ ቤተሰብ በመሆን የሚሰጠው ክህነት (Royal priesthood) ነው፡፡ ለመሆኑ እንዴት ነው ምዕመናን የእግዚአብሔር ካህናት ሊሰኙ የሚችሉት?
1.የክርስቶስ የአካሉ ክፍሎች በመሆናቸው የምናገኘው ክህነት 
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በክርስቶስ አምነን ስንጠመቅ የእርሱ የአካሉ ሕዋሳት እንደምንሆን ሲጽፍልን “እኛ ሁላችንም በአንድ መንፈስ አንድ አካል ለመሆን ተጠመቀናል … እንግዲህ እናንተ የክርስቶስ አካሉ ናችሁ ፤ እያንዳንዳችሁም የአካል ክፍሎች ናችሁ፡፡”(1ቆሮ.12፡14-27) ይለናል ፡፡ ስለዚህ እኛ በእርሱ ቸርነት በመንፈስ ቅዱስ ሥራ በጥምቀት አካሉ ሆነናልና ሐዋርያው “እንግዲህ ወደ ሰማያት የወጣ ታላቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን”(ዕብ.8፡14) እንዲል የክህነቱ ተካፋዮች ሆነናል ፡፡ ቢሆንም እንዲህ ሲባል በየግላችን ካህናት መሆን ይቻለናል ማለታችን ግን አይደለም፡፡ ነገር ግን እያንዳንዳችን በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ  እንደ አንድ አካል በመሆን አንዱን አካል ክርስቶስን በማገልገል ስንተጋ በእርሱ አካል በኩል ካህናት እንባላለን ፡፡ 
 ይህን የክህነት ዓይነት ከጳጳስ እስከ ምዕመን ድረስ የሚካፈለው የክህነት ዓይነት ነው ፡፡ ምክንያቱም ሁሉም በጥምቀት የአንዱ የክርስቶስ የአካሉ ክፍሎች ሆነዋልና ፡፡ ስለዚህም ነው ቅዱስ ጴጥሮስ“በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ”(1ጴጥ.2፡4)ማለቱ፡፡ አንድ ክርስቲያን የዚህ ክህነት ተካፋይ ሆኖ እንዲዘልቅ ከተፈለገ መጠመቁ ብቻውን አይጠቅመውም ፡፡ ይልቁኑ አስቀድሞ ራሱን ከነውር ሁሉ በመጠበቅና ከመንፈስ ቅዱስ ያገኘውን ጸጋ በመረዳት በዚያ ጸጋ ተጠቅሞ የጠፋውን የሰውን ልጅ ከኃጠአት በመመለስ ክርስቶስን ሊያገለግልና ክርስቲያን ማኅበረሰቡንም እንደ አካል ክፍሉ ቆጥሮ ፍጹም በሆነ ፍቅር ሊወድ እንዲሁም ሊያስብለት ይገባዋል፡፡ 
ነገር ግን እርስ በእርሳችን በተግባር የተገለጠ ፍቅር ከሌለንና እንደተሰጠን ጸጋ መጠን የጠፋውን ወገን ለመመለስ የማንተጋ ከሆንን የእርሱ የክህነቱ ተካፋይ ልንሆን ይቅርና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እውነተኛው የወይን ግንድ እኔ ነኝ ፤ ተካዩም አባቴ ነው ፡፡ በእኔ ያለውን፣ ፍሬ የማያፈራውን ቅርጫፍም ሁሉ ያስወግደዋል”(ዮሐ.15፡1) ብሎ እንዳስተማረን ከእርሱ ኅብረት ተቆርጠን መጣላችን የማይቀር ነው ፡፡ ነገር ግን ከሁሉም ጋር በፍቅር የምንመላለስና በጥምቀት ባገኘነው የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የእርሱን ፈቃድ ለመፈጸም የምንተጋ ከሆንን የክህነቱ ተካፋዮች በመሆን መዳናችንን እናረጋግጣለን ፡፡ 
2. ሰውነታችንን ሕያውና ቅዱስ መሥዋዕት አድርገን በማቅረብ 
አንድ ሰው ተጠምቆ ክርስቲያን ከሆነ ወደፊት የራሱ አይደለም ነገር ግን ሐዋርያው “ለራሳችሁ አይደላችሁም በዋጋ ተገዝታችኋልና ስለዚህም እግዚአብሔርን በሥጋችሁ አክብሩት ፡፡”(1ቆሮ. 6፡19-20) እንዲል የክርስቶስ ባሪያ ነው ፡፡ ስለዚህም እኛ ወደፊት ለራሳችን አንኖርም፡፡ እርሱ ለእኛ እንደኖረ እኛም በሕይወታችን ዘመን ሁሉ እርሱን ለማገልገል እንኖራለን ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህን አስለመልክቶ ሲያስተምር “በሕይወት የሚኖሩት ስለ እነርሱ ቤዛ ሆኖ ለሞተውና ለተነሣውም እንጂ ወደፊት ለራሳቸው የሚኖሩ እንዳይሆኑ እርሱ ስለ ሁሉ ቤዛ ሆኖ ሞተ”(2ቆሮ.5፡ )ይለናል ፡፡ 
ስለዚህም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእኛ መዳን ራሱን መሥዋዕት አድርጎ እንዳቀረበ እንዲሁ እኛም ሰውነታችንን ከነውር ሁሉ ጠብቀን ለጽድቅ ሕይወት በመትጋት በእግዚአብሔር ፊት የተወደደ መሥዋዕት አድርገን ራሳችንን ልናቀርብ ተጠርተናል ፡፡ እንዲህም ስለሆነ ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ላይ “ወንድሞቻችን ሰውነታችሁን ለእግዚአብሔር ሕያውና ቅዱስ ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እማልዳችኋለው ፡፡ ይህም በእውቀት የሚሆን አገልግሎታችሁን ነው ፡፡”(ሮሜ.12፡1)በማለት አስተምሮናል፡፡
 በዚህ ኃይለ ቃል ሁለት መሠረታዊ ቁም ነገሮችን እናስተውላለን፡፡ አንደኛው እኛ ራሳችንን ለእግዚአብሔር ቅዱስና ሕያው መሥዋዕት አድርገን በማቅረባችን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መምሰላችን ነው፡፡ ጌታችን ስለእኛ መዳን ራሱን መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ እኛም ራሳችንን መሥዋዕት አድርገን እናቀርባለን፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ መሥዋዕትን ማቅረብ የሚችለው ካህን ብቻ ነው ፡፡ እኛም በዚህ ቦታ ራሳችንን መሥዋዕት አድርገን በማቅረባችን ካህናትን እንመስላቸዋለን፡፡ በዚህ ተግባራችን የክህነትን አገልግሎት እየፈጸምን ነው ፡፡ በዚህ ምክንያት ምዕመናን ምንም እንኳ አማናዊ የሆነውን የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለማቅረብ ሥልጣኑ ባይኖራቸውም ራሳቸውን ሕያውና ቅዱስ መሥዋዕት አድርገው ለእግዚአብሔር በማቅረባቸው ካህናት ይሰኛሉ ፡፡ እንዲህም ስለሆነ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ከላይ ያነሣናቸውን ቁምነገሮች አንድ ላይ በማድረግ “በሰው ወደ ተናቀ ፣ በእግዚአብሔር ግን ወደ ተመረጠውና ክቡር ወደ ሆነው ወደ ሕያው ድንጋይ ወደ እርሱ ቅረቡ፡፡ ደግሞም እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ” (1ጴጥ.2፡4) ብሎ አስተማረ ፡፡ 
እንዲህም ስለሆነ እኛ ክርስቲያኖች የቤተክርስቲያን ጉዳይ አያገባንም ልንል አንችልም ፡፡ አያገባንም የምንል ከሆነ የክርስቶስ የአካሉ ሕዋሳቶች ከመሆን ተቆርጠናል ማለት ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ማለት አንድም የምዕመናን ኅበረት ማለት ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ደግሞ ለክርስቶስ አካሉ ናት፡፡ ስለዚህም ቤተክርስቲያን ማለት እኛ፣ እኛ ማለት ቤተክርስቲያን ማለት ከሆነ የቤተክርስቲያን ጉዳይ በእርግጥም ያገባናል፡፡ ስለገዛ ሰውነታችን አያገባችሁም የሚል አላዋቂ ሰው ማን ነው? እንዲህ የሚል አካል ካለ በእርግጥ የአእምሮ ሕመምተኛ መሆን አለበት ፡፡ ስለዚህም የቤተክርስቲያን ሕመም ያመናል የእርሱዋም ኀዘን ያስከፋናል፡፡
 በተጨማሪም ቤተክርስቲያን ልትፈጽማቸው የሚገቡ ተግባራትን ሳትፈጽማቸው ቀርታ ከሆነ ለምን ብለን እንጠይቃለን፡፡ የክርስቶስ መንጋ ሲበተን ይከፋናል፤ አካላችን የሆነው ደሃው ሲጎሳቆል አንገታችንን እንደፋለን፤ ክፋያችን የሆነች እኅታችን በድህነት ምክንያት ከክብር ስታንስ በኃዘን ጦር እንወጋለን፡፡ የክርስቶስ መንጎች በተኩሎች ሲነጠቁ ልባችን በከባድ ኃዘን ይደማል ምክንያቱም የአንድ ክርስቲያን መጎዳት የኛም መጎዳት ነውና፡፡ የቤተክርስቲያን ጉዳይ አያገባንም የምንል ከሆነ የቤተክርስቲያንና የክርስቶስ ጠላቶች ሆነን እየተንቀሳቀስን ያለን የዲያብሎስ ማኅበርተኞች ሆነናል ማለት ነው፡፡ እኛ ግን እንዲህ አይደለንምና የቤተክርስቲያን ሕመም አኛንም ያመናል ስለዚህም ያገባናል፡፡
 በተቃራኒው ደግሞ ቤተክርስቲያን የሰውን ዘር ለክርስቶስ ስትማርክ ደሃውንና ደሃይቱን ስታስብ በድህነት ምክንያት ወደ ኃጢአት እንዳይገቡና ከከሃዲያንም ጎራ እንዳይቀላቀሉ ስትቤዣቸው ፣ ክርስቶስ ኢየሱስ ከእርሷ እንደሚጠብቀው መንጎቹዋን ስታሰማራ፣ ምዕመኖቹዋን በመቀደስ ለዓለም ብርሃን እንዲሆኑ ስታበቃ እንዲሁም እንደተሰጣቸው ጸጋ የጠፉትን እንዲያድኑ ስታሰማራቸው ስንመለከት ደስታችን ወሰን የለውም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “አንዱ የአካል ክፍል ቢታመም ከእርሱ ጋር የአካል ክፍሎች ሁሉ ይታመማሉ አንዱ የአካል ክፍል ደስ ቢለውም የአካል ክፍሎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል”(1ቆሮ.12፡26)ብሎ እንዳስተማረው የአንድ ምዕመን ሕመም እኛንም ያመናል በአንድ ሰው መዳን ልክ እንደ ቅዱሳን መላእክት በእኛም ዘንድ ታላቅ ደስታ ይሆናል፡፡ ስለዚህም ሁላችንም በተሰጠን ጸጋ ቤተክርስቲያንን ለማገልገል እንትጋ ምክንያቱም ሁላችን የክርስቶስ ካህናት ሆነናልና ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የተሰጠንን ጸጋ ለይተን በማወቅ እርሱን ለማገልገል ያብቃን ለዘለዓለሙ አሜን ፡፡   

1 comment:

  1. DN. BERTA LEBZU GIZE SITEYKEW YENEBEREWN TIYAKE MELESKLGN, EGZIABHER EJIHN YABERT!!!!

    ReplyDelete