በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
27/11/2009
እግዚአብሔር እኔ ነፍስን ልክ እንደ አዳምና ሔዋን ከእኔ ጋር አንድ አድርጎ የፈጠራትን ግዙፏን ሥጋዬን እንድረዳት አድርጎ ፈጠረኝ። ስለዚህ አምላኬ እርሷን እንደሚያውቃት መጠን አይሁን እንጂ ሥጋዬን አውቃታለሁ፡፡ ምድርን በእርሷ ላይና ውስጥ ያሉትን እንደማጥናት እንዲሁ ግዙፋን ሥጋዬን በማጥናት ሁል ጊዜ አዳዲስ የሆኑ ነገሮችን ከእርሷ እያወቅሁ እኖራለው፡፡ ለዕውቀቱ ፍጻሜ የለውም፤ ብቻ እርሷን ለማወቅ ተሰጥቶኛልና ስለእርሷ ማንነት መናገር ብዙም አይቸግረኝም፡፡ የሚደንቀኝ ግን ስለ ራሴን መርምሬ ለማወቅ አለመቻሌ ነው፡፡ ረቂቅ መንፈስ መሆኔን አውቃለሁ ነገር ግን አይቼ ዳስሼ አረጋግጬ አይደለም፡፡ መዓዛዬን፣ ቁመቴን፣ ውፍረቴን፣ ቅጥነቴን ገጽታዬን ጭምር አላውቀውም፡፡ በአጠቃላይ መንፈስ መሆኔን እንጂ ለሌላው ማንነቴ ባይተዋር ነኝ፡፡ የሚደንቀው ግን መላእክት እርሷን ማወቃቸው ነው፡፡
ቅዱሱ መጽሐፍ የሚነግረኝ መንፈስ ቅዱስ በአፍንጫዬ እፍ ተብሎ በእርሱ ሕያው እንደሆንኹ ነው፡፡ ደምም ማደሪያዬ እንደሆነ ተጽፎልኛል፡፡ ደም ደግሞ በሁሉም የሰውነት ክፍሎቼ ውስጥ ይገኛል፡፡ እንዲህም ሲባል በሰውነቴ መጠንና ልክ ሙሉ ሆኜ እንደምኖር ለመግለጥ የተነገረ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ ሥጋ በሕይወት ለመቆየት በሰውነት ውስጥ ያለው የደም ዑደትና የደሙ መጠን ወሳኝ ነው፡፡ የደም ዑደቱ ከተቋረጠ ያ የደም ዑደቱ የተቋረጠበት አካል በድን ይሆናል፤ ከሰውነትም ተቆርጦ ይወድቃል፡፡ ወይም ደም ከሰውነት ፈሶ ካለቀ ወይም በበቂ ሁኔታ ከሌለ ፈጥኖ ለሕልፈተ ሕይወት ያደርሳል፡፡ ይህን አውቃለሁ፡፡ የሰውነትን ሥርዓት የሚያዛባ አንድ ነገር ካለ በተለይ የደም ዝውውርን የሚያቋርጥ ነገር ከተከሰተ እኔ ነፍስ ከሥጋ ፈጥኜ እለያለሁ፡፡ ምክንያቱም ምንም የምሠራው የለኝምና፡፡ ያኔ የእግዚአብሔር ጥሪ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ የሚደንቀኝ ግን እኔ የራሴን መንፈስ የሆነ አካል መጠንና ልክ አለማወቄ ነው፡፡
ይህ ብቻ ግን አይደለም የሰውን ነፍስ ተመልክቼ እኔ ምን እንደምመስል አለመረዳቴ ቁዝም ያደርገኛል፡፡ ቢሆንም ግን ውስጣዊ ሰውነት የሚላት ነፍሴ እንደ ሥጋ ሁሉ የራሷ የሆነ አካል እንዳላት ዐይን፣ ጆሮ፣ እጅ፣ እግር፣ እንዲሁም ሌሎችም የሰውነት ክፍሎች እንዳሏት መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጌ እረዳለሁ፤ እንደ ሥጋ አካላት እንደማይሆን ግን እርግጠኛ ነኝ፡፡ ለምሳሌ ለሕልፈት በማይዳርግ መልኩ አንዱ የሥጋ አካሌ ቢቆረጥ እኔ ነፍስም ተደርቤ የምቆረጥ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን በዚያ ሥፍራ እኔ አለሁን? ብዬ ራሴን ብጠይቅ መልሱ አላውቅም ነው፡፡ ምክንያቱም ሥጋዬ በሌለበት እኔ በዚያ ሥፍራ ስለመገኘቴ የሚጠቁም አንዳች ነገር አላገኝምና፡፡ ብቻ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ አያድርገውና የሥጋ እግሬ ብትቆጥ መንፈስ የሆነው እግሬ በዚያ መኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ እንደምረዳውም ለዚህ ጉዳት የተዳረጉ ወገኖቼ የነፍሳቸው እግር በቦታው እንዳለ ፈጽመው አይገነዘቡም ባዶ እንደሆነ ይረዳሉ እንጂ፡፡ ይህ በእርግጥ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ እናም የነፍስ ተፈጥሮ እንደ አምላክ አይሁን እንጂ የማይመረመር እንደሆነ ተረዳሁ፡፡ መላእክትን እኛ እናውቃቸዋለን፡፡ እነርሱም እኛን ያውቁናል፡፡ እኛ ራሳችንን አናውቅም እነርሱ ግን ራሳቸውን ያውቃሉ፡፡ ይህም ግርም የሚል ነገር ነው፡፡
ቢሆንም ግን ክብር ለእርሱ ለወደደን ይሁንና ቢያንስ ስለ ራሴ መጠነኛ መረዳት እንዲኖረኝ መጽሐፍ ቅዱስ አግዞኛልና እርሱን አምላኬን አመሰግነዋለሁ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡- እስራኤላውያን እንደ አሕዛብ ንጉሥ አልነበራቸውም ነበር፡፡ በእነርሱ ላይ የነገሠው እግዚአብሔር ነበር፤ የሚመራቸውም በሊቀ ካህናቱ በኩል ነበር፡፡ ነገር ግን ካህናቱ የገዛ ሆዳቸው በልጦባቸው ሕዝቡን ስላስመረሩት ሕዝቡ በሽማግሌዎቹ በኩል “እነሆ፥ አንተ ሸምግለሃል፥ ልጆችህም በመንገድህ አይሄዱም፤ አሁንም እንደ አሕዛብ ሁሉ የሚፈርድልን ንጉሥ አድርግልን አሉት”(1ሳሙ.8፡5) ጥያቄአቸው ሊቀ ካህናት የነበረውን ሳሙኤልን ቢያዝንም እግዚአብሔርም “በእነርሱ ላይ እንዳልነግሥ እኔን እንጂ አንተን አልናቁምና በሚሉህ ነገር ሁሉ የሕዝቡን ቃል ስማ” በማለት በእነርሱ ማዘኑን ቢገልጥም ፈቃዳቸውን ግን ከመፈጸም አልተመለሰም ነበር፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ጉልበተኛው ደካማውን፣ ብልጣብልጡ የዋህዉን የሚገዛባትን ለድሃና ለአቅመ ደካሞች የማይመቸውን አውሬአዊ ሥርዓት ለመረጣቸው ሕዝቦች ሊሰጥ ፈቃደኛ አይደለም፡፡ ስለዚህ ሕዘቡ ያደረገውን ወገን በመላእክት ሥርዓት እርሱ ንጉሣቸው እነርሱ ሕዝቦቹ እንዲሆኑ ሲል እንደ አሕዛብ ነገሥታትን አያስነሣባቸውም፡፡ ነገር ግን እስራኤል እግዚአብሔርን ሳያስቀድም በአሕዛብ ያየውን ከላይ ሲያዩት የሚያምረውን ሥርዓት በእጅጉ ናፈቀ፡፡ እግዚአብሔርም ምርጫቸው ትክክል አለመሆን ሊያስረዳቸው ሲል በሳሙኤል “በእናንተ ላይ የሚነግሠው የንጉሡ ወግ ይህ ነው፤ ወንዶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሰረገለኞችና ፈረሰኞች ያደርጋቸዋል፥ በሰረገሎቹም ፊት ይሮጣሉ፤ ለራሱም የሻለቆችና የመቶ አለቆች ያደርጋቸዋል፤ እርሻውንም የሚያርሱ እህሉንም የሚያጭዱ የጦር መሣሪያውንና የሰረገሎቹንም ዕቃ የሚሠሩ ይሆናሉ፡፡ ሴቶች ልጆቻችሁንም ወስዶ ሽቶ ቀማሚዎችና ወጥቤቶች አበዛዎችም ያደርጋቸዋል፡፡ ከእርሻችሁና ከወይናችሁም መልካም መልካሙን ወስዶ ለሎሌዎቹ ይሰጣቸዋል።ከዘራችሁና ከወይናችሁም አሥራት ወስዶ ለጃንደረቦቹና ለሎሌዎቹ ይሰጣቸዋል፡፡ ሎሌዎቻችሁንና ገረዶቻችሁን፥ ከከብቶቻችሁና ከአህዮቻችሁም መልካም መልካሞቹን ወስዶ ያሠራቸዋል፡፡ ከበጎቻችሁና ከፍየሎቻችሁ ዐሥራት ይወስዳል፤ እናንተም ባሪያዎች ትሆኑታላችሁ፡፡ በዚያም ቀን ለእናንተ ከመረጣችሁት ከንጉሣችሁ የተነሣ ትጮኻላችሁ፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር አይሰማችሁም።” ብሎ ተናገራቸው፡፡”(1ሳሙ.8፡11-18) እስቲ አስቡት ከዚህ የበለጠ ጽኑ ባርነት አለን? አስቲ መላልሳችሁ አንብቡት፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ቤተ መቅደሱን የሚያገለግሉ የሳሙኤል ልጆች ሕዝቡን አስመርረውታልና ሕዝቡ በውሳኔው ጨክኖ “የሳሙኤልን ነገር ይሰማ ዘንድ እንቢ አለ፡፡ እንዲህ አይሁን፥ ነገር ግን ንጉሥ ይሁንልን፥ እኛም ደግሞ እንደ አሕዛብ ሁሉ እንሆናለን፤ ንጉሣችንም ይፈርድልናል፥ በፊታችንም ወጥቶ ስለ እኛ ይዋጋል አሉት፡፡(1ሳሙ.8፡19)
ሳሙኤልም ሕዝቡ እንዳመረረ ተረድቶ ከቢንያም ወገን የሆነውን “ሳኦልን እንደ ምርጫቸው ቀብቶ አነገሠባቸው” ነገር ግን የካህኑ ሳሙኤል ድጋፍ ከሳኦል አልራቀም ነበር፡፡ ቢሆንም ግን የንጉሥ ሳኦል እምቢተኝነት ብዙም ሳይቆይ መገለጥ ጀመረ፤ ሳሙኤል እግዚአብሔር ያዘዘውን ትእዛዝ ሳይሰማ ለሆዱ አድልቶ አማሌቃውያንን ጨርሶ ከማጥፋት ተመለሰ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔርም ፍልስጤማውያን በእርሱ ላይ እንዲበረቱ አደረጋቸው፤ ሠራዊቱንና ልጆቹን ሁሉ ፈጁ እርሱና ጥቂቶች ብቻ ቀሩ፡፡
በዚህ ሁኔታ ሳለ እግዚአብሔርን ጠየቀ እግዚአብሔርም በሕልምና በኡሪም ወይም በነቢያት አልመለሰለትም፡፡ በጊዜውም ሊቀ ካህናት ሳሙኤል አርፎ ነበር፡፡ ስለዚህ ሳኦል ሳሙኤልን ያገኘው ዘንድ ሽቶ ቀድሞ ያጠፋቸው የነበሩትን መናፍስት ጠሪዎችን ፍለጋ ወጣ ፡፡ አንዲት መናፍስት ጠሪ በዓይንዶር እንዳለች ሰምቶ ራሱን ሰውሮ ወደ እርሷ ሄደ፡፡ መናፍስት ጠሪዋንም ሳሙኤልን እንድታስነሣለት ጠየቃት ቢሆንም ግን እርሷ ሳታሟርት ገና ቃሉ ከሳኦል አፍ እንደወጣ እግዚአብሔር የነቢዩን የሳሙኤልን ነፍስ ካለችበት አወጣት፤ ከእርሱ ጋር ሌሌች መናፍስት ነበሩ፡፡ ያቺ መናፍስት ጠሪም ይህን ትይንት ለማየት በቃች፤ በእጅጉም ደንግጣ ጮኻ በሳሙኤል ሳኦልን አውቃ አንተ ሳኦል ስትሆን ለምን አታለልኸኝ ብላ ተናገረችው፡፡ ሳኦልም ምን እንዳየች እንድትነግረው ጠየቃት እርሷም “አማልክት ከምድር ሲወጡ አየው አለችው” መልኩን ጠየቃት “ሽማግሌ ሰው ወጣ፤ መጐናጸፊያም ተጐናጽፎአል አለች” እርሱም ሳሙኤል እንደሆነ ተረዳ፡፡ እርሱ ግን ለማየት አልበቃም፡፡ ቢሆንም ተጎንብሶ ሳሙኤልን እጅ ነሣው፡፡ ሳሙኤልንም ያናግረው ጀመር፡፡ ሳኦል እንዲህ አለ “ፍልስጤማውያን አይለውብኛል እግዚአብሔርም ትቶኛል የማደርገውን ትነግረኝ ዘንድ ጠራሁህ አለው” ሳሙኤልም “የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማህምና፥ በአማሌቅም ላይ ታላቅ የሆነ ቍጣውን አላደረግህምና ስለዚህ ዛሬ እግዚአብሔር ይህን ነገር አድርጎብሃል”(1ሳሙ.28፡18)ብሎ መለሰለት፡፡ ፍልሴማውያን አየሉበት ሦስቱን ልጆቹን ገደሉአቸው እርሱንም አቆሰሉት ስለዚህ ጋሻጃግሬውን እነዚህ ቆላፎች መጥተው እንዳይወጉኝና እንዳይሳለቁብኝ ሰይፍህን መዝዘህ ውጋን አለው፤ ጋሻጃሬውም ሰይፉን መዝዞ ገደለው፡፡ በዚህ መልክ የሳኦል ንግሥና ፍጻሜ ሆነ፡፡
ወገኖቼ በዚህ ሥፍራ ምን ልብ አላችሁ ? ስለ ሳሙኤልስ ነፍስ ምን ተረዳችሁ? ነፍሱ እግዚአብሔር ያጎናጸፋትን መጎናጸፊያ ተጎናጽፋለች የራሷ የሆነ ሰዋዊ አካልና ቅርጽ ነበራት ነገር ግን ረቂቅ ስለሆነች ሳኦል ለማየት አልበቃም፡፡ ለዚያች መናፍስት ጠሪዋ ግን ዳግም ወደዚህ ክፉ ተግባር እንዳትመለስ ተግሣጽ እንዲሆናት፣ ነፍሳትን የማስነሣት ስልጣኑ የእርሱ እንጂ የእርሷ እንዳልሆነ ትረዳ ዘንድ የሳሙኤል ነፍስ ከሲኦል አውጥቶ ከነክብሩ አሳያት፡፡የሳሙኤል ነፍስመም በሲኦልም ሆና በእግዚአብሔር ጥበቃ ሥር ስለነበረች ሳሙኤል ሳኦልን “ለምን አወክኸኝ ለምንስ አስነሣኸኝ? አለው” ከሳኦልም ጋር ተነጋገረ፡፡ ይህንን ልብ በሉ፡፡ በዚህም ነፍስ የራሷ አካል እንዳላት የምትሰማ የምታይ ዓይኖችም እንዳሏት አስተውሉ፡፡ ስለዚህ ነፍስ የራሷ የሆነ አካል እንዳላት ወደ አምላኳ ስትሄድ እንደ ግብሯ ለእርሷ የሚስማማ የክብር ወይም የውረደት ካባን እንድትጎናጸፍ በሳሙኤል መረዳት እንችላለን፡፡ ቢሆንም ግን በትንሣኤ ይህቺ የተሰወረችው ማንነቴ በክርስቶስ ሆና እንደማያት አውቃለሁ፡፡ አሁንም ከበቃሁ እንደ ወንጌላዊው ዮሐንስ ነፍሳትን በበጉ ፊት ቆመው እርሱን ሲያመሰግኑት፤ ኃጥአንን ሲካሰሱ እመለከት ይሆናል፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ፈንታ ቢሆንም ግን አሁን ለማየት ያልተቻለኝን ማንነቴን ጊዜ ይፍጅ እንጂ ለማየት እንደምበቃ ተረድቻለሁ፡፡ ይህ እምነት ነው፡፡ እምነቴንም በትንሣኤ እውን ይሆናል፡፡ እንዲህ አነጋጋሪና ረቀቅ አድርጎ በአርአያውና በአምሳሉ ለፈጠረኝ ለሥላሴ ክብር ምሳጋና ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን ፡፡
No comments:
Post a Comment