በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
05/04/2004 ዓ.ም
ክርስትና ማለት ክርስቶስ ማለት ነው፤ ክርስቶስም ክርስትና ማለት ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ሰው ተፀንሶ በመወለድ፣ በየጥቂቱ አደገ መጽሐፍ እንዲል ኃጢአትን እስከ ሞት ድረስ ተቃወመ፡፡ ክርስትናም እንዲሁ ናት ተፀንሳ ልትወለድ በየጥቂቱም ልታድግ ኃጢአትን በመቃወም እስከሞት ልትጸና ይገባታል፡፡
ክርስትና ማለት ክርስቶስ፣ ክርስቶስ ማለት ክርስትና ማለት ነው፤ ቤተሰብም ቤተክርስቲያን ማለት ነው፡፡ ቤተክርስቲያንም በቅድስት ድንግል ማርያም ትመሰላለች፤ ስለዚህ ቤተሰብ ቅድስት ድንግል ማርያምን ሊመስል ይገባዋል፡፡ እርሱዋ እግዚአብሔር ከወላጆች ሊገኝ የሚገባው መንፈሳዊ ብስለት ውስጥ ስለነበረች ክርስቶስን ለ...መውለድ ተመረጠች፡፡ የእርሱዋ ቤተሰብን በመንፈሳዊ እውቀት የመምራት ብቃቱዋን ለማስረዳት ለእኛ “በሰውም በእግዚአብሔርም ፊት በጥበብና በሞገስ እንዲሁም በቁመት አደገ” ተብሎ ጻፈልን፡፡ እርሱዋ የእውነተኞች ወላጆች ምሳሌ ናት፡፡ ቤተሰብና ቤተክርስቲያን እንዲሁ ልጆቻቸውን ክርስቶስን መስለው እንዲያድጉ በሰውም በእግዚአብሔርም ፊት በጥበብና በሞገስ በጤንነትም የማሳደግ ሓላፊነት አለባቸው፡፡ ይህ ሕይወት ክርስትና ይባላል፡፡
ወይም ክርስትና እንደ መስቀሉና ክርስቶስ ናት፡፡ መስቀልን ስናስብ ጌታችንን አምላካችንን ከልደቱ እስከሞቱ ለእኛ አብነት የሆነባቸውን ተግባራዊ የሕይወት ምልልሶችን እናስባለን፡፡ መስቀልን ከክርስቶስ ክርስቶስንም ከመስቀል ነጣጥለን እንዳናስብ ክርስትናንም ከክርስቶስ ክርስቶስንም ከክርስትና ነጣጥለን አናስብም፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም “ስቅለቱ የእርሱን ልደት ሲያውጅ ልደቱ ደግሞ የእርሱን ሞት ያውጃል” ብሎ ያስተምራል፡፡ ክርስቶስ በሥጋ ከእውነተኛይቱ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም ካልተወለደ እንዴት ሊሞት ይችላል? እርሱ ሊሰቀል የሚገባው ከሆነ በሥጋ ሊወለድ ግድ ነው፡፡ምክንያቱም መለኮት በባሕርይው ሞት የለበትምና፡፡ ስለዚህ አንዱ ለአንዱ ማስረጃ ሆነ፡፡ ልደቱን ስናስብ ኃጢአትን በመቃወም ክርስቶስን ወደ ማወቅ ልናድግ እንጂ ልደቱን አሳበን የኃጢአት ፈቃዳችንን ልንፈጽም አይደለም፡፡ ቤተሰብ የክርስትና ሕይወታችን መሠረት ነውና እናንተ ወላጆች ሆይ ቅድስት ድንግል ማርያምን ምሰሉዋት፡፡ ልጆቻችሁን በመንፈሳዊ ጥበብና እውቀት አበልጽጋችሁ ክርስቶስን ለብሰው እንዲያድጉ ትጉ፡፡ ንጹሕና ቅዱስ የሆነውን አዲሱን ሰው ክርስቶስን እወቁት ምሰሉት! ክርስትና ይህቺ ናት፡፡ ክርስቶስ በእኛ ይገለጥ ዘንድ በልደቱ እርሱን በመምሰል እስከሞት ድረስ ኃጢአትን በመቃወም እንኑር፡፡ መልካም የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት ይሁንልን አሜን!!