Wednesday, January 25, 2012

በእውን እግዚአብሔር በሰዎች ልጆች ላይ ፍትሐዊ ነውን?(ቅዱስ ይስሐቅ)



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
17/05/2004
 ስለእግዚአብሔር ብሎ ማጣትን በፍጹም ፈቃደኝነትና ደስታ የተቀበለ ሰው እርሱ በውስጡ ንጹሕ የሆነ ሰው ነው፡፡ የሰውን ስህተት የማይመለከት እርሱ በእውነት አርነት የወጣ ሰው ነው፡፡ ከሰው በሚቀርብለት ክብር ያልተደሰተ እርሱንም በማያከብሩት ያልተከፋ ሰው እርሱ ለዚህ ዓለምና ለምድራዊ አኗኗር የሞተ ሰው ነው ፡፡ ማስተዋል ለሰዎች ከተሠሩላቸው ሕግጋት ሁሉ እጅግ የላቀና በየትኛውም ደረጃ እና መመዘኛ ሥራን በአግባቡ ለማከናወን ዓይነተኛ መሣሪያ ነው ፡፡ ኃጢአተኛውን አትጥላው እኛ ሁላችን የኃጢአትን ሸክም የተሸከምን በደለኞች ነንና ፡፡
 ስለ እግዚአብሔር ብለህ እርሱን ለመቃወም ከተነሣህ ግን ስለ እርሱ አልቅስለት ፡፡ ስለምን እርሱን ትጠላዋለህ? ኃጢአቱን ጥላ  ስለእርሱም መመለስ ጸልይለት ፡፡ እንዲህ በማድረግ በኃጢአተኞች ላይ ያለተቆጣውን ነገር ግን ስለእነርሱ መዳን የጸለየውን ክርስቶስን ምሰለው፡፡ ስለኢየሩሳሌም መጥፋት እንዴት እንዳለቀሰ አትመለከትምን ? በብዙ ድክመቶቻችን የተነሣ ሰይጣን በእኛ ላይ ያፌዝብናል ፡፡ በእኛ ላይ በሚያፌዘው ሰይጣን የሚፌዝበትን ወንድማችንን ስለምን እንጠላዋለን? ሰው ሆይ ስለምን እንዲህ ይሆናል ? ኃጢአተኛን መጥላት ትፈልጋለህ እርሱ እንዳንተ ጻድቅ መሆን ይሣነዋልን ? ፍቅር ሳይኖርህ የአንተ ቅድስና ምን ይጠቅምሃል ? ስለእርሱ ስለምን አታነባም ? ነገር ግን አንተ እርሱን ታሳድደዋለህ ፡፡ አንዳንዶች በኃጥአን ላይ ባለማስተዋል በቁጣ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የኃጢአተኞችንም ሥራ ለይተው የሚያውቁ አድርገው በራሳቸው  ይታመናሉ፡፡