Wednesday, October 16, 2013

ምንኩስናና ትዳር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች


05/02/2006
በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ


ክርስትና ለሰይጣን ይገዛ ከነበረ ዓለም ወጥቶ እርሱ የጽድቅ ጸሐይ የሆነው ክርስቶስ ብርሃን ሆኖት በቀን እንጂ በጨለማ የማንመላለስበት የቀን ልጅ ተሁኖ የሚኖርበት ሕይወት ነው፡፡ ክርስትና ከክርስቶስ ጋር ተሰቅለን ነፍስ በምትሰጠው ሕይወት ሳይሆን ለዘለዓለም አባ አባ ብለን የምንጠራበትን መንፈስ በሰጠን በመንፈስ ቅዱስ ሕያዋን ሆነን የምንኖርበት ሕይወት ነው፡፡ ስለዚህም ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር ራሳችንን ለጽድቅ ሥራ ያጨን ደናግላን ነን፡፡ አገባንም አላገባንም ለክርስቶስ የታጨን በመሆናችን ደናግላን ነን፡፡ ይህ ድንግልና የሚጠፋው ክርስቶስን ክደን በሰይጣን ሕያዋን ሆነን የኖርን ሰዓት ነው፡፡ቢሆንም ግን ይህም ቢሆን በንሥሐ የሚታደስ ድንግልና ነው፡፡ ጌታ ጠፍተን እንድንቀር የማይወድ ከኃጢአታችን ይልቅ መጥፋታችን የሚያሳዝነው በንስሐ በተመለስን ጊዜም በደስታ እጆቹን ዘርግቶ በፍቅር የሚቀበለን አምላክ ነው፡፡