Thursday, November 29, 2012

በድንግል ማርያም እናትነት ወንድምነትና እኅትነት ለእኛም



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
21/03/2005

አንዳንዶች ባይረዱት ነው እንጂ ቅድስት ድንግል ማርያም ለምድራዊቱ ቤተክርስቲያን ወይም ቤተክርስቲያን ለተሰኘነው ለእኛ አብነት የሆነች አማናዊቱ ቤተክርስቲያን ናት፡፡እኛም በእርሱዋ ተመስለን ለክርስቶስ ሙሽሪትም፣ እናቱም፣ ወንድምና እኅቱም፣ አገልጋዩም፣ ልጁም ተብለናል፡፡(ማቴ.12፡50) በእርሱዋም ለጌታ የታጨን እናቶች፣ ወንድሞችና እኅቶች እንዲሁም አገልጋዮችና ልጆች ስለሆንን ጠላት ዲያብሎስ ሁሌም ያሳድደናል፡፡ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለክርስቶስ እንዲሁ ናት፡፡እርሱዋ ለእርሱ እናቱ ብቻ አልነበረችም ሰውነቱዋን ለእርሱ ማደሪያነት ያጭች እኅቱም፣ አገልጋዩም፣ ልጁም ነበረች፡፡ እርሱዋ የቤተክርስቲያን አማናይቱ ምሳሌ ናት፡፡ እኛም በክርስቶስ ቤተክርስቲያን ተሰኝተናል፡፡ ስለዚህም ሰይጣን “በአንተና በሴቲቱ መካከል በዘሩዋና በዘርህ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ”(ዘፍ.3፡15) የሚለው ቃል በእኛ ላይም ተፈጽሞ ጠላት ዲያብሎስ ዘምቶብናል፡፡



እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ታቦተ ጽዮን



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
ኅዳር 20/2004 በማኅበረ ቅዱሳን ድኅረ ገጽ የተለቀቀ ጽሑፍ

እግዚአብሔር አምላክ ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ካወጣቸው በኋላ የአምልኮ ሥርዐታትን ይፈጽሙበት ዘንድ የምስክሩን ድንኳን፣ የቃል ኪዳኗ ታቦትንና ለአምልኮ ሥርዐቱ ማከናወኛ የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ ንዋያተ ቅድሳትን እንዲሠሩ በሙሴ በኩል አዝዞአቸው ነበር፡፡ ከቃል ኪዳኗ ታቦት ውስጥም በእግዚአብሔር ጣት ዐሥርቱ ትእዛዛት የተጻፉበት የሕጉ ጽላት፣ አርባ ዓመት ሙሉ እስራኤላውያን በሲና ምድረ በዳ የተመገቡትን መና የያዘች መሶበ-ወርቅ፣ አሮን ለክህነት አገልግሎት ስለመመረጡ ምስክር የሆነችው ለምልማና ፍሬ አፍርታ የተገኘችው የአሮን በትር ይገኙባታል፡፡(ዕብ.9፡4)

ታቦተ ጽዮን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትመሰላለች፡፡ ይህን ለመረዳት ግን ስለ ታቦተ ጽዮን አሠራርና መንፈሳዊ ትርጉም አስቀድመን ልንረዳ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ታቦተ ጽዮንን እንዲሠራ ብልሃትን፣ ጥበብን፣ ማስተዋልን፣ ዕውቀትን ይለይ ዘንድ መንፈሱን ያሳደረበትን ከይሁዳ ወገን የሆነውን ባስልኤልን መረጠ ፡፡(ዘፀ.25፡9) እርሱም እግዚአብሔር በሰጠው ማስተዋል ከማይነቅዝ እንጨት ርዝመቷ ሁለት ክንድ ተኩል፤ ወርዱዋም አንድ ክንድ ተኩል፣ ቁመቷም አንድ ክንድ ተኩል እንዲኖራት አድርጎ ታቦቷን ሠራት፡፡ በመቀጠል በውስጥም በውጪም በጥሩ ወርቅ ለበጣት፣ ከታቦቷም ዙሪያ የወርቅ አክሊልን አደረገላት፡፡ ካህናት ታቦተ ጽዮንን ለመሸከም እንዲረዳቸውም በአራቱም መዓዘናት በወርቅ የተሠሩ ቀለበቶችንና በእነርሱም ውስጥ የሚገቡ ሁለት መሎጊያዎችን ሠራ፡፡ ከጥሩ ወርቅም የስርየት መክደኛውን በቃል ኪዳን ታቦቷ ላይ በርዝመቷና በወርደዋ ልክ ሠራ፡፡ የስርየት መክደኛውን እንዲጋርዱት አድርጎም ጥሩ ከሆነ ከተቀጠቀጠ ወርቅ ኪሩቤልን ሠራ፤ በስርየት መክደኛው ግራና ቀኝም አደረጋቸው፡፡ እነዚህ በጥሩ ወርቅ የተሠሩት ሁለቱ ኪሩቤል ፊታቸው ወደ ስርየት መክደኛው ሆኖ እርስ በእርሳቸው የሚተያዩ ተደርገው የተሠሩ ናቸው ፡፡ በዚህ በስርየት መክደኛው በሁለቱ ኪሩቤል መካከል  እግዚአብሔር ለሙሴ በመገለጥ ሰው ከባልንጀራው እንደሚነጋገር ያነጋግረው ነበር፤ ለሕዝቡ በደመና አምድ ይታያቸው ነበር፡፡(ዘፀ.25፡22፤33፡8-11)