Monday, January 16, 2012

በእውን ሰው በመበደሉ መንፈስ ቅዱስ ይለየዋልን?




ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
 07/04/2004 ዓ.ም
አዲስ አበባ
መግቢያ
 ፊሊክስዩስ በሰሜናዊ ሶርያ ለምትገኝ ማቡግ ለምትባል ቤተክርስቲያን ጳጳስ የነበረ አባት ሲሆን ፤ በዘመኑ በጣም ታዋቂ የሆነ የነገረ-መለኮት ሊቅ ነበር፡፡ የኬልቄዶንን ጉባኤ በመቃወም በሶርያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተጠቃሽ የሆነ አባት ሲሆን እርሱ የኬልቄዶንን ጉባኤን የመቃወሙ ምክንያት የኬልቄዶናውያን አስተምሀሮ መለኮትን ከትስብእት ለመነጣጠልና ለመለያየት የሚሞክር ትምህርት ነው በማለት ነበር፡፡ አብዛኛዎቹ የእርሱ ጽሑፎች በነገረ መለኮት ላይ ያተኮሩ ቢሆኑም የሥነ ምግባር ትምህርቶችንም አብዝቶ ጽፎልናል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ይህን ይመስላል፡፡
“ከእግዚአብሐር የተቀበልነው መንፈስ ቅዱስ የነፍሳችን ነፍስ ነው፡፡ ስለዚህም  ጌታችን በሐዋርያት ላይ እፍ በማለት መንፈስ ቅዱስን አሳደረባቸው፡፡ በእነርሱም መንፈስ ቅዱስ የነፍሳችን ነፍስ ይሆን ዘንድ ለእኛ ተሰጠ፡፡ በተፈጥሮአዊዋ ነፍስ ነፍስ ይሆን ዘንድ መንፈስ ቅዱስን ተቀበልን፡፡ ልክ ነፍሳችን የሥጋችን ሕይወት እንደሆነች፤ መንፈስ ቅዱስም የነፍሳችን ሕይወት ማድረግ እንደሚገባን ለማስገንዘብ ለነፍሳችን ነፍስ ይሆን ዘንድ በጥምቀት መንፈስ ቅዱስን ተቀበልን፡፡ ከአዳም የተሰጠችው ሕይወት ከእግዚአብሔር እስትንፋስ የተገኘች ነበረች፡፡ “የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት” ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ ይህም መንፈስ ቅዱስ ነበር፡፡ ነገር ግን በመተላለፈ ከእርሱ ተወሰደ፡፡(ዘፍ.፪፥፯)