Tuesday, January 1, 2013

የፍጥረት ሁሉ ናፍቆት እነሆ ከሴት ብቻ ተወለደ



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
24/04/2005
የፍጥረት ሁሉ ናፍቆት የሆነውን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በዐይነ ሥጋ ለማየት ዘመነ ዘመናት ተቆጥረው ለልደቱ 15 ዓመታት ሲቀሩት በቅድስት ድንግል ማርያም እድሜ የልደቱ ዘመን ተካቶ ተቆጠረ፡፡ የሰው ልጆች ሁሉ የድኀነትን ቀን ናፍቀው ዐይኖቻቸው በዚህች ድንግል ብላቴና መወለድና ማደግ ላይ ትኩረታቸውን አድርገው ነበር፡፡
እነሆ ከላይ ከአርያም የምስራቹ ቃል በመልእክተኛው በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም መጣ፡፡ እርሱዋም “እነሆኝ የጌታዬ ባሪያ እንደ ቃልህ ይደረግልኝ” ብላ በድንግልና ጸንሳ ዘጠኝ ወር በማኅፀኗ ተሸክማ በድንግልና ወለደችው፡፡ እረኞች የእረኞችን አለቃ ተመልከተው ደስ አላቸው፡፡ ሰብአ ሰግል በደስታ ለአምላክ የሚቀርበውን ወርቅ እጣን ከርቤ አቀረቡለት በፊቱም ወድቀው ሰገዱለት፡፡ መላእክትም “ስብሐት ለእግዚአብሔር ሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ” እያሉ አመሰገኑ ሰማያውያን ከምድራውያን ጋር ምስጋናን አቀረቡ፡፡ ፍጥረት ሁሉ በደስታ ሰከረ፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያምም በቀደሞይቱ ሔዋን ምትክ የሕያዋን ሁሉ እናት ሆነችልን፡፡ እኛም በጥምቀት እርሱን በመልበስ የእርሱ ወንድሞችና እኅቶች ተባልን፡፡ በእርሱም የቅድስት ድንግል ማርያም ልጆች ተሰኘን፡፡ ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ ሃሌ ሉያ!!!