በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
29/10/2004
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ጴጥሮስ …ትወደኛለህን? ብሎ ከጠየቀውና እርሱም አዎን ብሎ ከመለሰ በኋላ “... ግልገሎቼን አሰማራ…ጠቦቶቼን ጠብቅ … በጎቼን አሰማራ” ብሎ መንጋውን እንዲጠብቅ አደራ እንደሰጠው እናውቃልን፡፡(ዮሐ.19፡15-17)ይህ
ሓላፊነት ምንም እንኳ ለእርሱ ይነገረው እንጂ ለሐዋርያት ሁሉ የተሰጠ ሓላፊነት ነበር፡፡ እነርሱም የክርስቶስን መንጋ ከሥጋና ከመንፈስ
ርሃብ ጠብቀው የድርሻቸውን ተወጥተው አልፈዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ማለት ሕጻናት፣ ወጣቶችና አረጋዊያን በአንድነት የሚኖሩባት፣ በምድር ያለች ግን ሰማያዊት፤ ቅዱሳን መላእክት፣ ቅዱሳን ነፍሳትና በምድር ያለነው በጥምቀት ከክርስቶስ ጋር በሞቱ ለዚህ ዓለም ኃጢአት የሞትን፤ መንፈስ ቅዱስ በሚሰጠን ሕይወት ሕያዋን የሆንንና በትንሣኤ ሕይወት የምንመላለስ የምንኖርባት፤ ጌታችን መድኀኒታችን የሚገዛትና የሚመራት ከምድር እስከ ሰማይ የተተከለች ዘለዓለማዊት መንግሥት ናት፡፡ ገዳም ግን መነኩሳት በፈቃድ የብሕትውናን ሕይወት መርጠው የሚኖሩባትና ለእነርሱ ብቻ የምትስማማ ሆና ሥርዐት የተበጀላት መንፈሳዊት ሥፍራ ናት፡፡