ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
26/09/2004
መግቢያ
ለቅዱስ ኤፍሬምና ለሌሎችም የሶርያ
ቅዱሳን አባቶች ጦም፣ ጸሎት እንዲሁም ምጽዋት ለነፍስ እንደ ብርሃን ናቸው፡፡ ዐይን ያለ ብርሃን ድጋፍ እንደማታይ እንዲሁ ነፍስም
ያለእነዚህ ድጋፍ መንፈሳዊውን ዓለም መረዳት አትችልም፡፡ ጌታችንም “እንግዲህ ዐይንህ ጤናማ ብትሆን ሰውነትህ ብሩህ ይሆናል፡፡
ዐይንህ ግን ታማሚ ብትሆን ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል፡፡ እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ ጨለማውስ እንዴት ይበረታ!”(ማቴ.6፡22)በማለት
ብርሃን ያላቸው እነዚህን ነው፡፡ እነዚህን በአግባቡና ከከንቱ ውዳሴ ተጠብቀን የፈጸመናቸው ከሆነ መንፈሳዊ ማስተዋላችን እጅግ የጠለቀ
ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ነገር ግን እነዚህን ከሰው ክብርን በመሻት የፈጸምናቸው ከሆነ እነዚሁ ራሳቸው መልሰው ያጠፉናል፡፡
እነዚህ በአግባቡ ካልተገለገልንባቸው
በኃጢአትችን ላይ ኃጢአትን እንድንጨምር
ያደርጉናል፡፡ ስለዚህ በእኛ ያለው ብርሃን (ጦም፣ጸሎት፤ እንዲሁም ምጽዋት) በከንቱ ውዳሴና በሌሎችም ኃጢአት ጨለማ ከሆነ በፊት
ከፈጸምናቸው ኃጢአት ጋር ተደምረው እኛን ወደ ጥልቁ ጨለማ ይጥሉናል፡፡ ስለዚህም ነው ጌታችን “ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ
ጨለማውስ እንዴት ይበረታ” ማለቱ፡፡ ይህን ድንቅ የሆነ አስተምህሮ እንድታስተውሉትና እኔ በትርጉሙ እንደተደነቅሁ በእናንተም ትደነቁ ዘንድ ቅዱስ ኤፍሬም ወንጌላትን ከተረጎመበት መጽሐፉ ያገኘሁትን ትርጓሜ እነሆ ብያችኋለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ መጽሐፉን ገዝቶ በመላክ
የተባበረኝን ወንደሜን ሙሉጌታ ሙላቱን ከልቤ ላመሰግነው እወዳለሁ፡፡
ጌታችን ጦማችን ምን መምሰል እንዳለበት
ሲያስተምር “እንደ ጦመኛ እንዳትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል” አለን፡፡(ማቴ.6፡18)