ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
26/09/2004
መግቢያ
ለቅዱስ ኤፍሬምና ለሌሎችም የሶርያ
ቅዱሳን አባቶች ጦም፣ ጸሎት እንዲሁም ምጽዋት ለነፍስ እንደ ብርሃን ናቸው፡፡ ዐይን ያለ ብርሃን ድጋፍ እንደማታይ እንዲሁ ነፍስም
ያለእነዚህ ድጋፍ መንፈሳዊውን ዓለም መረዳት አትችልም፡፡ ጌታችንም “እንግዲህ ዐይንህ ጤናማ ብትሆን ሰውነትህ ብሩህ ይሆናል፡፡
ዐይንህ ግን ታማሚ ብትሆን ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል፡፡ እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ ጨለማውስ እንዴት ይበረታ!”(ማቴ.6፡22)በማለት
ብርሃን ያላቸው እነዚህን ነው፡፡ እነዚህን በአግባቡና ከከንቱ ውዳሴ ተጠብቀን የፈጸመናቸው ከሆነ መንፈሳዊ ማስተዋላችን እጅግ የጠለቀ
ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ነገር ግን እነዚህን ከሰው ክብርን በመሻት የፈጸምናቸው ከሆነ እነዚሁ ራሳቸው መልሰው ያጠፉናል፡፡
እነዚህ በአግባቡ ካልተገለገልንባቸው
በኃጢአትችን ላይ ኃጢአትን እንድንጨምር
ያደርጉናል፡፡ ስለዚህ በእኛ ያለው ብርሃን (ጦም፣ጸሎት፤ እንዲሁም ምጽዋት) በከንቱ ውዳሴና በሌሎችም ኃጢአት ጨለማ ከሆነ በፊት
ከፈጸምናቸው ኃጢአት ጋር ተደምረው እኛን ወደ ጥልቁ ጨለማ ይጥሉናል፡፡ ስለዚህም ነው ጌታችን “ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ
ጨለማውስ እንዴት ይበረታ” ማለቱ፡፡ ይህን ድንቅ የሆነ አስተምህሮ እንድታስተውሉትና እኔ በትርጉሙ እንደተደነቅሁ በእናንተም ትደነቁ ዘንድ ቅዱስ ኤፍሬም ወንጌላትን ከተረጎመበት መጽሐፉ ያገኘሁትን ትርጓሜ እነሆ ብያችኋለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ መጽሐፉን ገዝቶ በመላክ
የተባበረኝን ወንደሜን ሙሉጌታ ሙላቱን ከልቤ ላመሰግነው እወዳለሁ፡፡
ጌታችን ጦማችን ምን መምሰል እንዳለበት
ሲያስተምር “እንደ ጦመኛ እንዳትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል” አለን፡፡(ማቴ.6፡18)
የመጀመሪያውና ሁለተኛውን ትርጉም ጌታችን በግልጥ አስቀምጦታል፡፡ የመጀመሪያው ስትጦሙ ከሰው ዘንድ ክብርንና ምስጋናን እናገኛለን
ብላችሁ የምትጦሙ ከሆነ ከአምላክ ዘንድ አንዳች ዋጋ አታገኙም ሲለን ነው፤ ሁለተኛው ትርጉሙ ደግሞ በማይታየው እግዚአብሔር ፊት
ጦምን የሚጦም ሰው በስውር የሚያየው አምላኩ በግልጥ ይከፍለዋል ሲለን ነው፡፡ ስለዚህ “አንተ ግን ስትጦም በስውር ላለው አባትህ
እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል” አለን፡፡
እንዲህም ስለሆነ እግዚአብሔር ቃል ይህን ደግ ስጦታውን ትቀበል ዘንድ ጋብዞሃል፡፡ አእምሮህን በእግዚአብሔርዊ እውቀት የቀባኸውና ነፍስህን በንስሐ ውኃ ከኃጢአት ሁሉ ያጠራሃት ከሆነ እግዚአብሔር ለቅዱሳኖቹ ያዘጋጃትን ዐይን ያላያትን ጆሮም ያልሰማትን በረከት ይሰጥሃል፡፡ ስለዚህም በሰውነትህ ሕዋሳቶች ሁሉ ይህን እንደ መመሪያ ተቀበለህ ከነፍስህ ኃጢአትን አስወግድ፡፡ ራስህንም የቅድስናን ዘይት ቀባት፤ እንዲህ በማድረግህ የመሲሕው ክርስቶስ ወዳጅ ትባላለህ፡፡ አስከትሎም ጌታችን፡-
እንዲህም ስለሆነ እግዚአብሔር ቃል ይህን ደግ ስጦታውን ትቀበል ዘንድ ጋብዞሃል፡፡ አእምሮህን በእግዚአብሔርዊ እውቀት የቀባኸውና ነፍስህን በንስሐ ውኃ ከኃጢአት ሁሉ ያጠራሃት ከሆነ እግዚአብሔር ለቅዱሳኖቹ ያዘጋጃትን ዐይን ያላያትን ጆሮም ያልሰማትን በረከት ይሰጥሃል፡፡ ስለዚህም በሰውነትህ ሕዋሳቶች ሁሉ ይህን እንደ መመሪያ ተቀበለህ ከነፍስህ ኃጢአትን አስወግድ፡፡ ራስህንም የቅድስናን ዘይት ቀባት፤ እንዲህ በማድረግህ የመሲሕው ክርስቶስ ወዳጅ ትባላለህ፡፡ አስከትሎም ጌታችን፡-
“እንግዲህ ዐይንህ ጤናማ ብትሆን
ሰውነትህ ብሩህ ይሆናል፡፡ ዐይንህ ግን ታማሚ ብትሆን ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል”(ማቴ.6፡22)አለን፡፡ እንዲህ ሲል ለአንተ ልክ
እንደ ዐይኖችህ ብርሃን በሆኑት ጦምህና ምጽዋትህ ከበደልክ፤ በኃጢአትህ ምክንያት ያገኘህ ድንቁርናና አለማስተዋል እጥፍ ይሆንብሃል ሲለን ነው፡፡ ከሰው ምስጋናን ሽተህ የምትጦም ከሆነና የሰው ፊት አይተህ የምታደላ
ከሆነ ለነፍስ ዐይን እንደ ብርሃን በሆኑት በጦምህና በምጽዋትህ በበደልከው በደል
ምክንያት ከመጀመሪያው ኃጢአትህ ጋር ተደምሮ ቅጣትህን እጥፍ ድርብ ያደርግብሃል፡፡ ሴሰኝነትና እግዚአብሔርን መሳደብ ለከንቱ ውዳሴ
ብለን በምንጦመው ጦምና በአድሎ በምንፈጽመው ምጽዋት ምክንያት በእኛ ላይ የሚሰለጥኑብን ኃጢአቶች ናቸው፡፡
ጦምህና
ምጽዋትህ ሁለት ዋጋ አላቸው፡፡ ከሰው ክብርን ሽተህ የምትጦም ከሆነ
ኃጢአት በአንተ ላይ እንድትበረታ ደንቁርናህም እጅግ ጽኑ እንዲሆን እወቅ፡፡ ነገር ግን እጆችህን ለተቸገረ ሰው የምትዘረጋ ሕሊናህን
ግን ወደ አምላክ የምታነሣ ከሆነ፣ እንዲሁም ስትጦም ጦምህን በእግዚአብሔር ፊት ያደረግህ እንደሆነ ከፈጣሪህ ዘንድ መልካምን ዋጋ ትቀበላለህ፡፡
ይህ ኃይለ ቃል “ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና፡፡”(ማቴ.6፡21) ብሎ ጌታችን
ካስተማረው ትምህርት ጋር አንድ ዓይነት ትርጉም ያለው ነው፡፡
ጦምና ምጽዋታችን በከንቱ ፈቃዳችን ምክንያት
ለኃጢአት አሳልፎ እንዳይሰጠንና በደላችንንም እጥፍ ድርብ እንዳያደርግብን አምላካችን ይህን ማስተዋል ዘወትር ይሰጠን ዘንድ በዚህ የጦም ወር እንለምነው፡፡ ለወደደንና በእኛ ጥቂት ድካም ዘለዓለማዊ ዋጋን ለሚሰጠን ለእርሱ ምስጋና ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment