Wednesday, February 13, 2013

መንፈሳዊ እድገትና ተሃድሶ ይለያያሉ



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
07/06/2005
 መንፈሳዊ እድገት ማለት ታድሶ ማለት አይደለም፡፡ እኛ እኮ በክርስቶስ ታድሰን አዲሱን ሰው ክርስቶስን ለብሰናል ወይም ልክ እንደሙሉ ሕጻን አንድ ጊዜ ተወልደናል፡፡ የመጠን ያም ማለት የብስለት ለውጥ እንጂ የመልክ ወይም የማንነት ለውጥ የለንም፡፡ አሁን መልካችን ክርስቶስን መስሎአል በአዲስ ማንነት ደግሞ በሰማያዊ ልደት ተወልደናል፡፡ ከዚህ በኋላ ከእኛ የሚቀረው መንፈስ ቅዱስ በሚሰጠን ማስተዋል እየበሰልን ሙሉ ሰው ክርስቶስን ወደ መምሰል ማደግ ነው፡፡ የቤተክርስቲያንም ድርሻ መንጋዋን ዳግም በክርስቶስ ለተፈጠረበት መንፈሳዊ ከፍታ ማብቃት ነው፡፡ እርሱዋ ለልጆቹዋ እንደ እናት ናት፡፡
በእርሱዋ የተሟላ የሐዋርያትና የነቢያት ትምህርት አለ፡፡ በእነርሱ ውስጥ በጥምቀት ባደረውም መንፈስ ቅዱስ ክርስቶስን መስለው እንዲያድርጉ እንደየእድገታቸው መጠን ትመግባቸዋለች፡፡ መታደስ ማለት ይህን በአዲስ ተፈጥሮ በክርስቶስ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠምቀን አዲሱን ሰው ለብሰን የተፈጠርንበት ማንነታችን አርጅቶ እንደገና ወደ አዲስ ማምጣት ማለት አይደለም፡፡ እኛ እድሳታችን የተፈጸመው ልክ በመንፈሳዊ ልደት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠምቀን የእግዚአብሔር ልጆች ስንሆን ነው፡፡ ልጅ ከሆንን ደግሞ ቀስ በቀስ ማደግ አለብን፡፡ ይህም ከፍጹምነት ወደ ፍጹምነት ማለት ነው፡፡ ወይም ከሚበልጠው ወደ ሚበልጠው የመንፈሳዊ ብስለት ማደግ ነው ለዚህም ማለቂያ የለውም፡፡
 መንፈሳዊ ወተትን የሚጋቱ ሕጻናት አሉ ወተቱ ለእነርሱ መሠረታዊና እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን ጥርስ ባወጡ ጊዜ ጥሬን ወደ መቆርጠም አጥንትን ወደ መጋጥ ሲመጡ ጠንካራውን መንፈሳዊ ምግብምን ሊመገቡ ይገባቸዋል፡፡ በዚህም ውስጥ አንዳች ነውርም የለበትም፡፡ ነገር ግን በዚህ ብቻ አያቆምም በመንፈሳዊ ከፍታ ልንሸመግል ይገባናል፡፡ ያም ማለት ለመንፈሳዊ ትምህርት የመጀመሪያ የሆነውን ትምህርት አውቀን(ወተት) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩትን እውነታዎች በጥልቀት ተረድተን(ጠንካራውን ምግብ) ሙሉ ሰው በመሆን በመንፈስ ቅዱስ ወደ መመራት መድረስ መምጣት አለብን፡፡ ይህ ሁሉ ጤናማና በውስጡ አንዳች ነውር የሌለበት አካሉ በራሱ ሙሉ እንደሆነ የሚያድግበት መንፈሳዊ እድገት ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ግን በራሱዋ ሙሉ ናት ልጆቹዋን እነዚህን እየመገበች ታሳድጋቸዋለች፡፡ እንጂ በራሱዋ አትታደስም ቤተክርስቲያን ጥንትም ነበረች አሁንም አለች ወደፊትም ትኖራለች ምክንያቱም መሥራቹዋ ክርስቶስ መጋቢዋም መንፈስ ቅዱስ ዘለዓለማዊያን ናቸውና፡፡