Thursday, February 2, 2012

“ኑ ቤተክርስቲያንን ማርያም እንበላት”(ቅዱስ ኤፍሬም)

   


ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ 
25/05/2004 


"ማርያም መግደላዊት ትንሣኤውን ትመለከት ዘንድ ጌታ ወደ እርሱ አቀረባት፡፡
ስለምን ግን ጌታ ትንሣኤውን እርሱዋ ቀድማ እንድትመለከት አደረጋት? ስለምን ወንዶቹ እንዲመለከቱ አልፈቀደላቸውም?
ምክንያቱም ቤተ-ክርስቲያንና እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ያላቸውን የዝምድና ምስጢር ጌታችን ሊያሳየን በመፍቀዱ ነው፡፡
ጌታችን ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ቅድስት ድንግል ማርያም እርሱን በመፅነስ ቀድማ ተቀበለችው፤
ሞትን ድል አድርጎ ሲነሣ ደግሞ ትንሣኤውን መግደላዊት ማርያም አስቀድማ እንድትመለከት አደረጋት፤
በመጀመሪያውና በፍጻሜው(በልደቱና በትንሣኤው) ክቡር የሆነው የእናቱ ስም በዚያ እንደነበር ጮኾ ተናገረ፡፡
ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታን በመፅነስ በተቀበለችው ጊዜ መልአኩ ከፊቱዋ ነበር፤            
መግደላዊት ማርያምም እንዲሁ እርሱ ሕያው ሆኖ ባገኘችው ጊዜ መልአክ ከፊቱዋ ነበር፤ 
ስለዚህም ማርያም በቤተክርስቲያን ትመሠላለች፤
ድንግል ማርያም በወንጌል ቃል የሁሉ በኩር የሆነውን ልጇን በመውለዱዋ ደስ ተሰኘች፤
መግደላዊት ማርያምም በቤተክርስቲያን ቦታ ሆና ትንሣኤውን ተመልክታለችና ደስ ተሰኘች፤
ስለዚህም ቤተክርስቲያንና ቅድስት እናቱን ደስ ያሰኘው ሕፃን እርሱ በእውነት የተመሰገነ ይሁን”
ኑ ቤተክርስቲያንን “ማርያም” ብለን እንጥራት፤
ቤተክርስቲያንና ማርያም የሚሉት ስሞች በእውነት ለእርሱዋ የተገቡ ናቸውና፡፡
ለቤተክርስቲያን የመሠረት ድንጋይ ከተባለው ከቅዱስ ስምዖን ጴጥሮስ ቀድማ ማርያም ከመቃብሩ ዘንድ ተገኘች፤
 ቤተክርስቲያንንም ወክላ ጌታ እንደተነሣ የምሥራቹን ዜና ለስምዖን አመጣችለት፤
 ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቶአል ብላም ሰበከችለት፤
ማርያም ወደ ስምዖን ጴጥሮስ የትንሣኤውን ዜና ይዛ መምጣቱዋ አግባብነት ነበረው፤
ምክንያቱም እርሱ ለተመረጠችው ቤተ- ክርስቲያን አለትና መሠረት ነውና፡፡
… ኢሳይያስ “ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች”ብሎ የተናገረለሽ አማናይቱ ቤተክርስቲያን ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡
የልጅሽ ስም በራሱ ታላቅ የሆነ መልእክትን በውስጡ ይዞአል፤ ሁለት ስሞች በአንድ ላይ በመዋሐድ አማኑኤል የሚለውን ስም ሰጡ፤ ይህ ስም በቤተክርስቲያንና በክርስቶስ መካከል የሆነውን ተዋሕዶ የሚገለልጥ ስም ነው፤
እርሱ ካንቺ የነሣውን ሰብእና ገንዘቡ በማድረግ አንቺን ቤተክርስቲያን አሰኘሽ፡፡ እኛንም የአካሉ ክፍሎች በማድረግ ቤተክርቲያን አሰኘን፤ ስለዚህም "እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው" የሚለው የስሙ ትርጉም ባንቺና በእኛ እውን ሆነ፤
ከቅድስት እናቱ በነሣው ሰውነት በኩል እኛን ከራሱ ጋር በማዋሐድ ቤተክርስቲያን ላሰኘን ለእርሱ ለክርስቶስ ክብር ይሁን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

“ቁጣንና ሌሎችንም አስመልክቶ የቅዱስ ኤፍሬም ተግሣጽ”


(ስብከት ወተግሣጽ ዘቅዱስ ኤፍሬም ከሚለው መጽሐፌ የተወሰደ ነው፡፡)
24/05/2004
"አንተ መንፈሳዊ ተፈጥሮ አለህ፡፡ ነፍስህም የእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል ናት፡፡ እናም ከሰው ሁሉ ጋር በፍቅር በመኖር የእግዚአብሔር አርዓያ የሆነችውን ነፍስህን አክብራት፡፡ በምትኖርባቸው ዘመኖችህ ሁሉ በተቻለህ መጠን ሰውነትህን ከቁጣ ጠብቅ፡፡ ያለበለዚያ አንተን ወደ ሲኦል ታወርድሃለች፤ ጎዳናዎቿም ወደ ገሃነም የሚያመሩ ናቸው፡፡
እናም ቁጣን በልብህ አታኑራት፡፡ መራርነትንም በነፍስህ አታሳድር፡፡ በነፍሰህ ላይ አንዳች ሥልጣን የለህምና ነፍስህን መልካም በማድረግ ጠብቃት፡፡
አንተ በእግዚአብሔር ደም ወደ እርሱ ቀርበሃል፡፡ በክርስቶስ ሕማምም ድነኀል፤ አንተ በፈንታህ ለኃጢአት ሥራዎች የሞትክ ትሆን ዘንድ ስለአንተ መተላለፍ እርሱ ሞቷል፡፡ አይሁድ በመዘበት በፊቱ ላይ ምራቃቸውን ሲተፋበት መታገሡ ሰዎች ቢያፌዙብህ እንኳ እንድትታገሣቸው አርአያ ሊሆንህ ነው፡፡ መራራና ሆምጣጣ የሆነውን ወይን መጎንጨቱ ከቁጣ ትሸሽ ዘንድ ነው፡፡ በጅራፍ ተገርፎ በሰንሰለት ታስሮ መጎተቱ ስለጽድቅ ስትል መከራን እንዳትሰቀቅ ነው፡፡
ስለእውነት አንተ የእርሱ አገልጋይ ባሪያው ከሆንክ ቅዱስ የሆነውን ጌታህን ፍራው፡፡ ስለእውነት አንተ የእርሱ እውነተኛ ደቀመዝሙር ከሆንክ የመምህርን ፈለግ ተከተል፡፡ የክርስቶስ ወዳጅ ትባል ዘንድ ባልንጀራህ በአንተ ላይ ቢሳለቅ ታገሠው፡፡ ከመድኃኒዓለም የተለየህ እንዳትሆን በሰው ላይ ቁጣህን አትግለጥ፡፡