Monday, April 20, 2020

የልቡና ትንሣኤ - ወደ ነፍስ ትንሣኤ - የነፍስ ትንሣኤ - ወደ ሥጋና ለነፍስ ትንሣኤ

ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
12/08/2012
የልቡና ትንሣኤ ስለ እርሱ ማወቅን፣ መረዳትን፣ ማመንንና መቀበልን ይጠይቃል፡፡ ይህም ማለት ከውኃና ከመንፈስ ተወልጄ የእግዚአብሔር ልጅነትን አግኝቻለሁ፤ አሁን የምኖረው ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣው ከክርስቶስ ጋር በተዋሕዶ ነው፤ አሁን ከሰማያውያን ጋር ኅብረትን ፈጥሬአለሁ፤ ከአእላፍት ቅዱሳን መላእክት፣ ከቅዱሳት ነፍሳት ጋር አንድ ጉባኤ  ሆኜአለሁ፤ ምንም እንኳ በምድር ብኖር በሰማያዊ ሥፍራ ነኝ ብሎ ማወቅ፣ መረዳት፣ ማመን፣ መቀበል ማለት ነው፡፡ ይህን ማወቁ፣ መረዳቱ፣ ማመኑና መቀበሉ ከሌለን ባልታደሰው በቀበርነው በአሮጌው ማንነታችን ዕውር ድንብራችንን መጓዛችን እንቀጥላለን፡፡ ያኔ የሥጋ ሞት ያስፈራናል፣ ዕለታዊው ነገር ያስጨንቀናል፣ ዘለዓለም የምኖር ይመስለናል፣ በመብል በመጠጥ ደስታን ለማግኘት እንተጋለን፣ የእግዚአብሔርን ሕልውና ትርክት ይመስለናል እንጂ አናምንበትም፡፡ እነዚህ የልቡናን ትንሣኤ በማጣታችን በእኛ ላይ የሚሰለጥኑብን ናቸው፡፡ ነገር ግን የልቡናን ትንሣኤ ገንዘብ ስናደርግ ያለፈው የጨለማ ጉዞ፣ ያለማወቅ ጉዞ፣ የሥጋ ባርነት ጉዞአችን ሁሉ ትዝ እያሉን ይቆጩናል፡፡ ከፊት ለፊታችን ብዙ ሥራ እንደሚጠብቀን እንረዳለን፡፡ ገና መድረስ ካለብን ከፍታና መረዳት እንዳልደረስን፣ ሥጋችን የክርስቶስ ሥጋ ሆኖ በጥምቀት መለወጡን እንዳልተረዳነው ወደዚህም መረዳት ለመድረስ መትጋት እንዳለብን፣ ሕሊናችን ሁሌም ይህን  አሮጌውን ሰዋችንን ማለትም እንደ ሥጋ ፈቃድ መመላለሳችንን ገፍፈን እንደ መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ እንድንመላለስ እንዲያተጋን ማሳሰብን ገንዘብ እናደርጋለን፣ የክርስቶስ አካል የሆነውን ሥጋችንን ባሕርይ ለማወቅ እንተጋለን፡፡ በአጠቃላይ ወደ ነፍስ ትንሣኤ እንመጣለን፡፡

 የነፍስ ትንሣኤ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የምንገባበት፣ ነፍስ እንጂ ሥጋ ለነፍስ ሕይወቷ እንዳልሆነች፣ መብል መጠጥ ነፍስን እንደማያኖሯት በተግባር የምንረዳበት ነው፡፡ በዚህ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሥጋ አገዛዝ ያከትማል፣ ነገር ግን ወደሚገባት ወደተፈጠረችበት የቅድስና ከፍታ ለማደግ ረጅም ጉዞ እንደሚቀራት ትረዳለች፡፡ ነፍስ ስትነሣ ዙሪያዋን ያለውን ወደመረዳት ትመጣለች፤ እርሷን የሚመስሉ ረቂቃን መላእክትን ታውቃቸዋለች፤ ወይም እነርሱን ትመላለሳለች ፈቃዷ ከፈቃዳቸው ጋር አንድ ይሆናል፤ ሥጋችን ለነፍስ ፈቃድ ወደ መገዛት ስትመጣ፣ ንስሐ ትገባለች፤ ከምሥጢረ ቁርባን ለመካፈልና ንጽሕትና ብርህት ለመሆን ትፋጠናለች፡፡ አላዋቂነቷ ሰለሚያጨንቃት ቅዱሳት መጻሕፍትን አዘውትራ ወደ ማንበብና ወደ መመርመር ትሄዳለች፡፡ ባጣቻቸው ስታለቅስ ባገኘቻቸው ሐሴትን ታደርጋለች፣ ደስታዋ ዮሐንስ መጥምቅ የድንግልን ድምፅ ሰምቶ ጌታው ሊጎበኘው በመምጣቱ በማኅፀን እንደዘለለው ዓይነት ደስታ ነው፡፡ ከሰው መቀላቀልን ፣ የማይጠቅሙ ዓለማዊ ነገሮችን መስማትን፣ ከሰዎች ጋር ማኅበርተኛ መሆንን ትሸሻለች፤ ስለ ዓለሙም የሚያወራባትን አትወድም፣ ስትሰማ ከመጥላቷ የተነሣ ስትጨነከቅ ትታያለች፤ በዚህ ከፍታ ላይ ያለ ሰው ስለ እግዚአብሔርም ቢሆን ከሰው ጋር መነጋገርን አይፈቅድም፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ቃል ብቻ ሳይሆን ተናጋሪውንም ሰው በመመልከቱ ሐሳቡ ስለሚከፈል ነው፡፡ ከቅዱሳን መላእክት ጋር፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር፣ ከቅዱሳት ነፍሳት ጋር ፊት ለፊት ባይተያይም ልክ እንደ በርጠሜዎስ በዙሪያው እንዳሉ ይረዳል፡፡ እነርሱ ምንም እንኳ መልስ ባይሰጡት አንደበቱን ሳይከፍት በነፍሱ ሲያነጋግራቸው ይገኛል፡፡  ያደንቃል፣ ያመሰግናል፣ በሲቃም ያለቅሳል፡፡ ይህ ሰው ፈጽሞ ምድራዊውን ሕይወት የዘነጋ ስለሆነ ስለሚበላው ስለሚጠጣው ስለሚለብሰው ለማሰብ በተገደደ ጊዜ ሁሉ ውስጡ በቁጣ ይሞላል፡፡ ዘለዓለም አምላኩንና ሰማያዊውን ሕይወት እየዘከረ መኖርን ይመርጣል፣ ግን አይችልም፡፡ ወደ ላይ እንዳይነጠቅ ሥጋው ትጎትተዋለች፡፡ የሥጋንም ፈቃድ ሊሞላ ሲተጋ ነፍሱ ማግኘት ያለባትን ያጣች እየመሰለው ይተክዛል፡፡ ዓለሙ ይህን ሰው  አእምሮውን ያጣና ሰነፍ አድርጎ ይቆጥረዋል፤ ግን አይደለም፡፡ እነዚህን ሁለቱን ማለትም ነፍሱንና ሥጋውን አጣጥሞ የሚመራበት ጊዜ ግን ይመጣል፡፡ ያኔ እርሱ በዓለም እየኖረ ግን በዓለም ውስጥ አይደለም፤ ከሰው ጋር ቢቀላቀልም መንፈሳዊው ተመስጦው አይወሰድበትም፣ ቅዱስ ዳዊት “የሚሠራው ሁሉ ይከናወንለታል” እንዲል እንደ ዮሴፍ ሥራው ሁሉ የተቃና ይሆንለታል፡፡ ቢሆንም ግን ከተመሥጦ ከቶ አይወጣም፡፡ ለሰዉም እንደ ዳንኤል “የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት ሰው” ሆኖ ይገለጣል፡፡ በእርሱ እግዚአብሔር ይናገራል፡፡ አስቀድሞ ግን ይህን ላያስተውለው ይችላል፡፡ ነገር ግን እየቆየ ይረዳዋል፡፡ ቃሉ እንደ ነቢዩ ሳሙኤል ከመሬት ጠብ አትልም፡፡ የመጻሕፍት ትርጓሜያት ከእርሱ ዘንድ የተሰወሩ አይሆኑም፡፡ ቅዱሳን መላእከትና ነፍሳት ለእርሱ የተገለጡና ከእነርሱ ጋር የሚነጋገሩ ይሆናሉ፡፡ አምላክም ለእርሱ ይገለጣል፡፡ ከዚህም የብዙ ብዙ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ገንዘብ ያደርጋል፡፡ ይህ ግን ተምኔት አይደለም በትንሣኤ ዘጉባኤ ዓይናችን ተገልጦ የምናየው አሁን ግን በድንግዝግዝታ የምናውቀው ነው፡፡

በዚህ ጊዜ ነፍስ ብትጸድቅም ብትከፋም ጽድቋና በደሏ ጽኑ ይሆንላታል ወይም ይሆንባታል፡፡ ነገር ግን በእርሷ መዓርግ ላይ ካሉት በስተቀር ለሌሎች የተገለጠ አይሆንም፡፡ ወደ እግዚአብሔር ፍቅር፣ ወደ ትሕትና፣ ወደ ራስን ማዋረድ፣ ወደ አርምሞ፣ ተግባራዊ ክርስትናን ገንዘብ አድርጎ ወደ መማለስ፣ በነፍስ ወደ አምላክ ወደ መጮኽ፣ አምላክን ለማየት ወደመናፈቅ ትመጣለች፡፡ በጉዞዋ ላይ እንቅፋት የሆኑባትን ሁሉ በጥበብ ታልፋለች፡፡ ያኔ የቅድስና ሕይወትን ስለምትለማምደው የእግዚአብሔር መቅደሱ ትሆን ዘንድ የተፈጠረች ሥጋ ትከብራለች፡፡ የኃጢአት ልማዷንም ትተዋለች ንጽሕትና ጽርይት ትሆናለች፡፡ በመስታወት ቤት ውስጥ እንዳለ ሰው በእርሷ አካል ውስጥ ያደረው ጌታ ለሁሉ ይታያል፡፡ እርሷን የተመለከተ ሁሉ ጌታን ይመለከታል፡፡ ይህ የነፍስና የሥጋ ትንሣኤ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ያለ ክርስቲያን በእውነት ብፁዕ ነው፡፡ ግን ደግሞ የማይቻል ሳይሆን ይህን ገንዘብ አድርገን ዳግም የተፈጠርን ነንና ለሁሉ ክርስቲያን የሚቻል የሚመረጥ ነው፡፡ ይህም መልክአ እግዚአብሔር ይባላል፡፡ አቤቱ አምላካችን ማስተዋልን ስጠን አንተ የቀረበርከውን አሮጌውን ማንነታችንን ለብሰን እንደ ፍጥረታውያን እንዳንመላለስ እባክህ እርዳን፡፡ ሁሌም እንደ ነፍስ ፈቃድ እንመላለስ ዘንድ ፍቀድ፡፡ ሥጋችን የአንተ መቅደስ መሆኗ በተግባር ይገለጥ ዘንድ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment