Friday, September 28, 2012

ስለንስሐ የተላከ መልእክት



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
18/01/2005
ውድ እና ከእግዚአብሔር ጋር ያለህን ሕብረት በእጅጉ የምናፍቅልህ ወገኔ ሆይ እንደምን አለህልኝ? ውድ ክርስቲያን ወገኔ ሆይ ንስሐ ማለት ሕመምን ለዶክተር እንደ መናገር ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው ሕመሙን ቢደብቅ ሕመሙ ወደማይደን ደረጃ ይለወጥና ነፍሱንም ሥጋውንም ያጠፋል፡፡ እንዲሁ በንስሐ መድኀኒትነት ከኃጢአት ቁስል ራሱን የማይፈውስ ክርስቲያንም ነፍሱንና ሥጋውን በገሃነም እሳት ያጠፋል፡፡ ውድ ክርስቲያን ወገኔ ሆይ! በክርስቶስ አምላክነት አምነን በመጠመቃችን ክብር ይግባውና ሁላችንም የክርስቶስ ወታደሮች ሆነናል፡፡ ስለዚህም ከኃጢአት ጋር በምናደርገው ፍልሚያ ልንቆስል እንችላለን፡፡ አንድ ቁስለኛ ደግሞ የሐኪም እርዳታ በእጅጉ ያስፈልገዋል፤ ያለበለዚያ ሕመሙን ቢደብቅ ቁስሉ ወደ ጋንግሪንነት ተለውጦ የማይድን ይሆንና በሞት ይወሰዳል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰው አንዴ ሞቷልና ሊድን አይችልም፡፡ ክርስቲያን ወገኔ ሆይ! ኃጢአት ለነፍሳችን እንደ በሽታ ነው፡፡በሽታ ጋር ደግሞ እንዲኖር የሚፈቅድ ሰው የለም፡፡ ስለዚህ ወደ ነፍሳችን መድኃኒት ወደ ክርሰቶስ ቅረብ፡፡ እርሱ ሕመምተኞችን እንጂ ጤነኞችን ሊፈውስ አልመጣምና፡፡(ማቴ.912) 
ወገኔ ሆይ ንስሐ ለመግባት አትፍራ፡፡ ወደ ካህን ስትቀርብ ወደ ክርስቶስ እንደቀረብክ ተረዳ፤ በእነርሱ አድሮ ይቅር የሚለን እርሱ ነው፡፡ ይህንን በምን እናረጋግጣለን ካልከኝ? ከታች እንደሚከተለው በጥቅስ አስደግፌ አቅርቤልሃለሁ፡፡

ጌታችን መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው  ደቀመዛሙርት አድርጓቸው፡፡ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፡፡›(ማቴ.2819-20)በሚለው ቃሉ ውስጥ ሥልጣን ለተመረጡ ሰዎች እንደሰጠና ከእነርሱም ጋር ዘወትር እንደሚኖር ገልጦልናል፡፡ እንዲህም እንደሆነ ቅዱስ ጳውሎስ አብነት ይሆነናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ከእርሱ ጋር ክርሰቶስ እንዳለ ሲያስረዳሁለተኛ በእናንተ ዘንድ በነበርኩ ዘንድ አሁንም ደግሞ በሩቅ ስሆን ክርስቶስ በእኔ አድሮ እንዲናገር ማስረጃ ከፈለጋችሁ እንደ ገና ብመጣ እንዳልራራላችው አስቀድመው ኃጢአት ላደረጉት ለሌሎችም ሁሉ አስቀድሜ ብዬአለሁ አስቀድሜም እላለሁ”ይለናል፡፡(2ቆሮ.132-4) በዚህ ኃይለ ቃል ውስጥ በጳውሎስ አካል ክርስቶስ ማደሩን እናስተውላለን፡፡
ክርስቶስ በጳውሎስ አካል ውስጥ የማደሩ ምሥጢር ቅዱስ በመሆኑ የተነሣ ሳይሆን የክህነት ሥልጣኑ ስለነበረው ነው፡፡ ይህንን ደግሞ ሲያስረዳጌታ እናንተን ለማነጽ እንጂ ለማፍረስ ያይደለ በሰጠው በሥልጣናችን ከፊት ይልቅ ብመካ እንኳ አላፍርምይለናል፡፡(2ቆሮ.108) ሥልጣኑ ምን እንደሆነ ማወቅ ከፈለግህ ደግሞእናንተ ይቅር ያላችሁትን እኔ ይቅር እለዋለሁ፡፡ እኔም ይቅር ካልሁ ይቅር ያልሁትን ስለእናንተ በክርሰቶስ ፊት ይቅር ብያለሁ(2ቆሮ.210)ይላል፡፡ በዚህ ጥቅስ  ውስጥ ሐዋርያው የተሰጠውን ሥልጣን መጠቀሙን እናስተውላለን፡፡
ይህ ሥልጣን አስቀድሞ 12 ሐዋርያት የተሰጠ ሥልጣን ስለመሆኑ “…አብ እንደላከኝ እናንተንም እልካችኋለሁ አላቸው፡፡ ይህን ብሎ እፍ ለባቸውና፦ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባችዋል አላቸውተብሎ ተጽፎልናል፡፡ (ዮሐ.2022)
ይህ ሥልጣን በሐዋርያት ብቻ የቀረ እንዳልሆነ እንድንረዳው ደግሞበገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” ብሎናል፡፡ (የሐዋ.2028) ሥልጣናቸው ደግሞ ከሐዋርያት ሥልጣን ጋር የተስተካከለ ሥልጣን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያስረዳ ቅዱስ ጴጥሮስ እንግዲህ እኔ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ የክርሰቶስም መከራ ምስክር ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ በመካከላችሁ ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራለሁ፤ በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ” ይለናል፡፡ (1ጴጥሮ.51-2)
ይህ ሥልጣን እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ያገለግላል፡፡ ስለዚህም ሐዋርያት ሥልጣኑ ለሚገባቸው ሰዎች እጅ በመጫን አስተላልፈዋል፡፡(የሐዋ.818-19) እንዲህም ስለሆነ ነው ጌታችን ለሐወርያት ስለመጽአቱ በነገራቸው ጊዜ “ጌታ በቤተሰዎቹ ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው? ጌታ መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፅዑ ነው እውነት እላችኋለሁ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል”  ብሎ ማስተማሩ፡፡(ማቴ. 24፡45-47) ይህ እንግዲህ የሚስረዳው እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የሚነሡ በመንፈስ ቅዱስ የሚሾሙ ካህናት እንዳሉ ነው፡፡ ስለዚህም ከእነርሱ በኋላም የተነሡ የሐዋርያት ሥልጣንን የተረከቡ ጳጳሳት ለቤተክርስቲያን አገልግሎት ሲባል ካህናትን ይሾማሉ፡፡ ይህን በቅዱስ ጳውሎስ ቃል ማረጋገጥ እንችላለን፡፡  ቅዱስ ጳውሎስ “ሽማግሌዎችን አንድትሾም በቀርጤስ ተውሁህ” በማለት ካህናትን ይሾም ዘንድ ለቲቶ ሥልጣን እንደሰጠው እንረዳለን፡፡ እንዲሁም በማንም ላይ እጆችህን ፈጥነህ አትጫን”(1ጢሞ.522)የምለውም የሚያረጋግጠው ይኼንኑ ነው፡፡ 
ወደፊትም ሥልጣኑን ሊረከቡ የሚገባቸው ሰዎች እንዴት ያሉ መሆን እንዳለባቸው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስረዳ “…እንግዲህ ኤጴስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል…." (1ጢሞ.31) እንዲሁም ስለቀሳውስት ደግሞበየከተማው ደግሞ እኔ አንተን እንዳዘዝኩህ ቀሳውስትን እንድትሾም በቀርጤስ ተውኩህብሎናል፡፡ (ቲቶ.15) 
ይህ ሥልጣን ምንም እንኳ በሰው እጅ ይሰጥ እንጂ ሹመቱን የሚሰጣቸው ሥላሴ ነው፡፡ ስለመንፈስ ቅዱስ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ “(የሐዋ.2028) ይለናል፡፡ ስለ እግዚአብሔር ወልድ ደግሞ “እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎች ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው?”(ማቴ.2445-51) ይለናል፡፡ ስለ እግዚአብሔር አብም “እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶችን ሐዋርያት ሁለተኛም ነቢያትን ሦስተኛም አስተማሪዎችን… አድርጎአል” ይለናል፡፡(1ቆሮ.12፡28) እናም በአንድ ካህን ሹመት ላይ የሥላሴን ተሳትፎ አለ፡፡
ውድ ክርስቲያን ወገኔ ሆይ! ይህን ሁሉ ለአንተ መዘርዘሬ ለንስሐ ወደ ካህን ስትሄድ ወደ ክርስቶስ እንደቀረብክ እንድታስውል ስለፈለግሁ ነው፡፡ በእርግጥም እንዲህ ነውና፡፡ እርሱ ርኅሩኁ አባት ነው፡፡ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም ወደ እናንተ እመጣለሁ፡፡"እንዲሁም "….እኔ በአባቴ እንዳለሁ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ እኔም በእናንተ እንዳለሁ በዚያ ቀን ታውቃላችሁ” እንዲል እኛን ያለእረኛ የሚጥለን ጌታ የለንም፡፡(ዮሐ.1418-20)
አንድ ቅዱስ አባት የተናገረውን እዚህ ላይ ላንሣልህ፡- ይህ ቅዱስ ብዙ መጻሕፍትን የጻፈ ሰው ነው፡፡እንዲህ ይለናል፡- “ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ እንዲህ አለ ሰዎች እኔን ቢነቅፉኝ እንደበደል አልይዝባቸውም፡፡ ለአንድ ነገር ግን እጠነቀቃለሁ እርሱም በእኔ ያምኑ ዘንድ ነው፡፡ እኔ ከኃጢአቶቻቸው ይልቅ በእኔ ማመናቸውንና መመለሳቸውን እንዲሁም የእኔን ፈቃድ መፈጸማቸውን እመለከታለሁ ይላል” ይለናል፡፡ ማመን ማለት ማወቅና መታዘዝ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ማመን ከምግባር ይቀድማል፡፡ ሰው በልቡ ያመነበትን ወደ ተግባር መልሶ ይፈጸማል፡፡ ስለዚህ ማመን ይቀድማል ምግባር ይከተላል፡፡ ስለዚህም ነው ይህ ቅዱስ እምነትን ማስቀደሙ፡፡ ከጻድቁም ቃል መረዳት የምንችለው አምላካችን ከኃጢአታችን ይልቅ መመለሳችንን እንደሚናፍቅ ነው፡፡  
 ውድ ክርስቲያን ወገኔ ሆይ! ይህንን እውነታ ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ የገለጠው ነው !!! ተመልከት ወገኔ በዚያን ጊዜ አይሁድ እጅግ ርኅራኄ የጎደለው መከራ ቢያደርሱበትም ምን እንዳለ ስማ “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው”(ሉቃ.2334) ይህ እንዴት ያለ ፍቅር!! እንዴትስ ያለ ርኅራኄ ነው!! ውድ ወገኔ ሆይ እስቲ አስተውለው ጌታችን ጭካኔአቸውን አንድም አልተመለከተም ነገር ለእነርሱ በጎውን ጠየቀ፡፡
እግዚአብሔር ሁሌም ያው ነው አይለወጥም፡፡ እኛን እጅግ ይወደናል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶአልና”(ዮሐ.316) እንዲል ሐዋርያውም “… ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና መኳንንትም ሁሉ እንዲደረግ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ፡፡ ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነትን ወደማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው፡፡”(1ጢሞ.21-4) እንዲሁምገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለኃጢአተኞች ሞቶአልና፡፡ስለጻድቅ ሰው የሚሞት በጭንቅ ይገኛል፤ስለ ቸር ሰው ግን ሊሞት እንኳ የሚደፍር ምንአልባት ይገኝ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር ያስረዳል”(ሮሜ.56)እንዲል ለእኛ እጅግ ርኅሩኅ አምላክ ነው፡፡
እንግዲህ ውድ ወገኔ ሆይ ወደሚያፈቅርህ አምላክህ በባሪያው በካህኑ በኩል መቅረብን አትፍራ፡፡ የካህኑን ማንነት ፈጽሞ አትመልከት በእርሱ ያደረውንና አንተን የሚያገለግለውን የክርስቶስን ሥልጣን ተመልክተህ ቅረብ፤ የካህኑ ድርሻ ለክርስቶስ መሣሪያ መሆን ነውና፡፡
ውድ ክርስቲያን ወገኔ ሆይ! አንድ እንድትለው የምፈልገው ነገር አለኝ፡፡ ተመልከት ወገነኔ ክርሰቶስ ስለ ኢየሩሳሌምኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር ዶሮ ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብስ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ እናንተም አልወደዳችሁም››(ሉቃ.1334)ብሎ ነበር፡፡ በእውኑ ክርስቶስ እነርሱን ማዳንና መሰብሰብ ይሳነዋልን? አይሳነውም ነገር ግን የእነርሱ ለመዳን አለመፈለግ ከለከለው እንጂ፡፡ ስለዚህም ለእኛ መዳን የእኛ ፈቃድ ወሳኝ ነው፡፡ ለመዳን ደግሞ መቅረብ ተገቢ ነው፡፡እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ፡፡”(ዕብ.416)
እግዚአብሔር ይርዳህ፡ በፍቅሩም ይጎብህ በጸጋውም ያበርታህ፡፡ሰላምን ሁሉ እመኝልሃለሁ፡፡

1 comment:

  1. ይህ ሥልጣን ምንም እንኳ በሰው እጅ ይሰጥ እንጂ ሹመቱን የሚሰጣቸው ራሱ ክርስቶስ እና መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር አብም እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያስረዳን “መንፈስ ቅዱስ እናንተን ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ “(የሐዋ.20፡28) ይለናል፡፡ክርሰቶስም ሥልጣኑን እንደሚሰጥ “እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎች ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው?”(ማቴ.24፡45-51) ይለናል፡፡ እግዚአብሔር አብም “እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን አንዳንዶችን ሐዋርያት ሁለተኛም ነቢያትን ሦስተኛም አስተማሪዎችን… አድርጎአል” ይለናል፡፡(1ቆሮ.12፡28) እናም በአንድ ካህን ሹመት ላይ የሥላሴን ተሳትፎ አለ፡፡

    ReplyDelete