Tuesday, March 13, 2012

አንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት ይረዳው?








በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
04/07/2004
ይህን ጽሑፍ አንድ ወንድሜ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብን በተመለከተ ለጠየቀኝ ጥያቄ የሰጠሁት መልስ ነው፡፡ ይህም በዚህ ድኅረ ገጽ ላይ ይገኛል ነገር ግን ለሁሉ አንባቢያን እንዲደርስ በመፈለጌ ርእስ ሰጥቼ እንዲህ አቅርቤዋለሁ፡፡  
ውድ ወንድሜ ሆይ እርግጥ ነው መጽሐፍ ቅዱስን ወዲያው ለመረዳት አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም በአንድ ምዕራፍ ውስጥ ብዙ በይዘታቸው የተለያዩ መልእክቶች ስለሚተላለፉ ነው፡፡ ይህ የአንድ መንፈሳዊ መጽሐፍ ጠባይ ነው፡፡ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ዓይነት አጻጻፍ በጥንት ቅዱሳን አባቶች መጻሕፍት ላይ ይገኛል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደ አንድ ዛፍ ነው፡፡ ግንዱ አንድ ሲሆን ብዙ ቅርንጫፎችና እጅግ ብዙ ቅጠሎች ያሉት ሲሆን ፍሬው ግን ምንም በቁጥር አንዱ ቅርንጫፍ ከአንዱ ቅርንጫፍ ይበልጥ የሚያፈራ ቢሆን አንድ ነው፡፡ ይህን ላስረዳህ፡፡ ግንዱ አንድ እግዚአብሔር ነው፡፡ ወይም ሥሩ እግዚአብሔር አብ ነው ግንዱ ክርስቶስ ነው ለዛፉ ሕይወት የሚሆነውና ፍሬ እንዲሰጥ የሚያደርገው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡