Friday, January 20, 2012

ክርስቶስ ለእኛ ኦርቶዶክሳዊያን ማን ነው?



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
12/05/2004 
እርሱ የእግዚአብሔር በግ ነው፤ እርሱም መሥዋዕት ነው፤
እርሱ ስለብዙዎች ኃጢአት የተሠዋው ፍሪዳ ነው፤ እርሱ መሥዋዕቱን የሚያቀርብ ሊቀ ካህናት ነው፤መሥዋት ተቀባዩም እርሱ ነው፤
ስለእኛ መከራን የተቀበለው እርሱ ነው፤ ስለእኛም የራራልን እርሱ ነው፤
እርሱ ሙሽራ ነው ፤እርሱ ራሱ ሙሽሪትም ነው፡፡(ከእናታችን የነሣው ሥጋ ለጌታችን እንደሙሽሪት ነው፡፡ ይህ ሥጋ ግን አምላክ በመሆኑ ሙሽራ ሆነ፤ በሐዋርያትም እኛ ለእርሱ ታጨን፡፡ ስለዚህም እርሱ ሙሽራ ነው፤ እርሱ ራሱ ሙሽሪት ነው አልን)
እርሱ  የሰርጉ ቤት ነው፤ እርሱ ራሱ  የሰርግ ቤቱ አሳላፊ ነው፤
እርሱ ገነት ነው፤ እርሱ ራሱ የሕይወት ዛፍ ነው፤
እርሱ  ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም ነው፤ እርሱ ራሱ መቅደሳችንና ቅድስተ ቅዱሳናችን ነው
በውኆች የተመሰለው እርሱ ነው፤ እርሱ ራሱ እኛ የምንኖርበት ዓለማችን ነው፤
እርሱ  ምግባችን ነው፤ እርሱ ራሱ ስለድኅነታችን የሚመግበን መጋቢያችን ነው፤
እርሱ ሕያው የሆነው ሕብስት ነው፤ እርሱ የሕይወት ውኃችን ነው፤
እርሱ እውነተኛው የወይን ግንድ ነው፤ እርሱ ራሱ የደስታ ወይናችን ነው፤
እርሱ ዕንቁዋችን ነው፤ እርሱ ራሱ መዛግብታችን ነው፤
እርሱ መረባችን ነው፤ እርሱ ራሱ ተዋጊያችን ነው፤
እርሱ የጦር መሣሪያችን ነው፤ እርሱ ሁሉን ድል የሚነሣ ነው፤
እርሱ ግዝረታችን ነው፤ እርሱ ራሱ ሰንበታችንና ሕጋችን ነው፤
እርሱ የቅዱሳን ኅብረት ለሆነችው ቤተክርስቲያን ራስ ነው፤ እርሱ መልካሙ የስንዴ ቅንጣት ነው፤
እርሱ የወይን እርሻችን ነው፤ የእርሻውም ባለቤት እርሱ ነው፤
እርሱ ግርማችን ነው፤ እርሱ እምነታችን ነው፤
እርሱ ሰርጋችን ነው፤ እርሱ የሰርግ ልብሳችን ነው፤
እርሱ የሕይወት መንገዳችን ነው፤ እርሱ በራችን ነው፤
እርሱ የጽድቅ ፀሐያችን ነው፤ እርሱ የነፍሳችን ብርሃን ነው፤
እርሱ ሕይወት ነው፤ እርሱ መንግሥተ ሰማያት ነው፤
እርሱ መጀመሪያ የሌለው መጀመሪያ፣ መጨረሻ የሌለው መጨረሻ፣ አልፋና ኦሜጋ ነው፤
ስለዚህም እኛ ኦርቶዶክሳዊያን በክርስቶስ ከክርስቶስ ለክርስቶስ የሆንን የክርስቶስ ነን!!!

የጽሙና ሕይወት ወዳዱ ዮሐንስ ሶርያዊ ስለ ጥምቀት ያስተማረው ትምህርት


ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
11/05/2004


ሥጋዊው ማኅፀን የሚታይ ሥጋን ለብሰን እንድንወለድ በማድረግ ከዚህ ዓለም ፍጥረታት ቁጥር እንዲደምረንና የዚህን ዓለም ውበት ለማድነቅ እንደሚያበቃን እንዲሁ ጥምቀትም መንፈሳዊ ልደትን እንድንወለድበት የተዘጋጀ ማኅፀን ነውና ከሰማያውያን ፍጥረታት ጋር እንድንደመርና መንፈሳዊውን ዓለም ለማየትና ለማድነቅ እንድንበቃ ያደርገናል ፡፡ በሥጋ ካልተወለድን በቀር ግሩም የሆነውን የዚህን ዓለም ውበት ማየት እንደማንችል ሁሉ በጥምቀት ካልሆነ በቀር እውነተኛውን ዓለም ለማየት አንበቃም ፡፡ ጌታችን ለኒቆዲሞስ እንደተናገረው አንድ ሰው አስቀድሞ ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልምና ፡፡…(ዮሐ.፫፥፫)
ያልተጠመቀ ሰው በኃጢአት ምክንያት ልክ እንደሞተ ሰው የአካል መገጣጠሚያዎቹ የተለያዩ የሚከረፋና የሚሸት ሬሳ ነው ፡፡ ሥጋ በነፍስ ምክንያት ሕያው እንደምትሆን ነገር ግን ነፍስ ብትለያት ፈርሳና በስብሳ ወደ አፈርነቱዋ እንድትመለስ በክርስቶስ አምኖ ያለተጠመቀም ሰው እጣ ፈንታው ይህ ነው፡፡ በክርስቶስ የማዳን ሥራ በጥምቀት ይህ ሰው ክርስቶስን ቢለብሰው የእግዘአብሔር አርዓያንና አምሳልን ገንዘቡ ከማድረጉ በተጨማሪ  በነፍስ ምትክ መንፈስ ቅዱስ ነፍሱ ይሆንለታል፡፡ ስለዚህም በእግዚአብሔር ዘንድ ሕያ እንጂ ሙ አይባልም፡፡
 ቅዱስ ጳውሎስ “… እኛም በአዲስ ሕይወት እንመላለስ ዘንድ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን ፡፡”(ሮሜ.፮፥፬) እንዲሁም “ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችሁታል”(ገላ.፫፥፳፯) እንዲል ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ጠላትነት ጠፍቶ ከእርሱ ጋር ማኅበርተኞች ሆነናል፡፡  በክርስቶስም ሰውነት በኩል የመለኮቱ ተካፋዮች ሆነናል፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ ይህ እንደሆን ለማስረዳት “አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም ፤ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም ፤ወንድም ሴትም የለም ፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና”አለን ፡፡ ( ገላ.፫፥፳፰) ጥምቀትን ለእኛ በሞትህ በመመሥረት  ሕያዋን ያደረገኸን አምላካችን ሆይ ላንተ ክብር ይሁን!!!