Friday, December 21, 2012

አርምሞ (ለአንድ ወንድሜ የጻፈኩት)



ከዲ/ን ሽመልስ መርጊ
12/04/2005
አርምሞ ከራስ ጋር ለመሆን ጊዜን ከመስጠት የሚጀምር ነው፡፡ እንዲያው በባዶ ግን አይደለም፤ አስቀድሞ የግል ጊዜ ሊኖረን  ግድ ነው፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ዐይን ውስጥ ትንሽ ብናኝ ብትገባ እንደምትረበሽና እንደምትታወክ ከዚያም በላይ አንደምታለቅስ እንዲሁ ሕሊናም ጥቃቅን በምንላቸው ኃጢአቶች መረበሹና መታወኩ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ ሕሊናችን በኃጢአት ከተያዘ መረጋጋትን ገንዘባችን ማድረግ አይቻለንም፡፡
ነገር ግን ሕሊናችን ከኃጢአት ነጽቶ እርጋታን ገንዘቡ ሲያደርግ በጥሙና ሆነን ያለ አንዳች መደነቃቀፍ መንፈሳዊውን ዓለምና ምሥጢር ወደ መረዳት እንመጣለን፡፡ ስለዚህ ወደ ጥሙና ሕይወት ከመግባታችን በፊት አስቀድመን ለንስሐ ራሳችንን ማዘጋጀት አለብን በኋላም ንስሐ መግባት፡፡ በንስሐ የእግዚአብሔር ፍቅር በውስጣችን ይቀጣጠላል፡፡ በዚህም ምክንያት ስለእግዚአብሔር በጥልቀት ለማወቅ እጅግ እንጓጓለን፡፡ በዚህ ሰዓት ነው እንግዲህ የምናነባቸውን ምንባባትና የምንጸልያቸውን ጸሎታት መምረጥ ያለብን፡፡ ያለበለዚያ ፈጽሞ አርምሞን ገንዘባችን ማድረግ አይቻለንም፡፡ ስለዚህ ሌላውን የሚነቅፉና ለጠላት ጥፋትን የሚለምኑ ምንባባትንና ጸሎታትን ከማንበብ መከልከል ተገቢ ነው፡፡