Sunday, January 6, 2013

“በአፉ መሳም ይሳመኝ”



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
28/04/2005
በአፉ መሳም ይሳመኝ ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ መልካም ነውና፡፡”(ማኃ.1፡1) የሚለው ቃል በይሁዳ ቤተልሔም እነሆ ተፈጸመ፡፡ ይህ ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ለሰዎች የሚሰጠውን  ሰላምና ፍቅር እንዲሁም እርቅ የሚናፍቁ የነቢያትና የቅዱሳን የናፍቆት ቃል ነበር፡፡ “በአፉ” ሲል “በእግዚአብሔር ቃል” ሲለን ሲሆን “ይሳመኝ” ሲልም የእግዚአብሔር ቃልን ሰው መሆን መናፈቃቸውን የሚናገር ነው፡፡ እንዲህ ካልሆነ እንዴት በአፉ ሊስመን ይቻለው ነበር? ይህ ቃል እርቅ በሰዎችና በእግዚአብሔር መካከል መፈጸሙ የማይቀር መሆኑን የሚያውጅ የናፍቆት ቃል ነው፡፡

ለነፍሳችን ሁለተኛዋ ነፍስ (በቅዱስ ኤፍሬም)



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
28/04/2005
ወዳጄ ሆይ! እምነት ለነፍስህ ሁለተኛዋ ነፍስ እንደሆነች መርምርና እወቅ፡፡ ሥጋ በነፍስ እንድትቆም የነፍስም በሕይወት መኖር በእምነትህ ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ እምነትህን ብትክድ ወይም ከራስህ ብታርቃት ነፍስህ ምውት ትሆናለች፡፡ በዚህም መሠረት የሚሞት ሥጋችን በነፍስ ላይ ጥገኛ እንደሆነች ነፍሳችንም በእምነት ላይ ጥገኛ ናት፡፡ እምነትም በእግዚአብሔር አብና በመንፈስ ቅዱስ ሕያዋን ባደረገን በእውነተኛ ልጁ ላይ ጥገኛ ናት፡፡
በዚህም እውነት ሰው ነፍሱን በሰማያት ካሉት ጋር ያገናኛታል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰው በነፍሱ በሕይወት ይኖራል፡፡ በሥጋ ሰውነቱም ያያል ይመለከታል፡፡ እንዲሁ እኛም በእምነት በፍቅርና በጥበብ የእግዚአብሔር መልክ ገንዘባችን አድርገን ከመለኮቱ ተካፋይ እንሆናለህ፡፡ ስለዚህም በነፍሳችን የሞትን እንዳንሆን ይህን ድንቅ የሆነ ማሰሪያ እንዳንበጥስ ወይም ነፍሳችን ከእምነት ባዶ እንዳናደርጋት እንጠቀቅ፡፡ ጌታችን ይህን አስመልከቶ እንዲህ ብሎ አስተምሮናልና “ሙታናቸውንም እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው”(ማቴ.8፡22)