Saturday, March 24, 2012

ኑ መጽሐፍ ቅዱስን በቅዱስ ኤፍሬም የንባብ ስልት እናንብበው



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
15/07/2004
መጽሐፍ ቅዱስን ቅዱስ ኤፍሬም እንዴት መነበብ እንዳለበት ሲያስተምር እንዲህ ይላል፡- “ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በሦስት ዐይነት መንገድ ያነብቡታል፡፡ አንደኞቹ በስሜት ሆነው የሚያነቡ(with passion) ሲሆኑ የእነዚህ ወገኖች አነባበብ ፀሐይ በተኮሰች ጊዜ ሥር ስላልነበረው ደርቆና ጠውልጎ ፍሬ ሳያፈራ የቀረውን በጭንጫ መሬት ላይ የተዘራን ዘር ይመስላሉ፡፡(ማቴ.13፡20) ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእነዚህ ወገኖች እንደገለጠው ለጊዜው መጻሕፍትን አንብበው እውቀትን በመጨበጣቸው ደስ የሚሰኙ ሲሆኑ፤  ነገር ግን በውስጡ ተጽፈው ያሉትን በጎ ምግባራት ለመፈጸም ከብዶአቸው ከማንበብ የተመለሱ ወይም ከንባብ ተሰላችተው ያቆሙ ናቸው፡፡
 ሌሎቹ ደግሞ አዋቂዎች ለመባልና ለመራቀቅ ሲሉ የሚያነቡ ናቸው፡፡ ጉድለት ለማግኘትም ብለው የሚያነቡ አሉ (without Passion)፡፡ እነዚህ ወገኖች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን እውነት ከሌሎች ጋር ሊሟገቱበት እንጂ በውስጡ የያዘውን በጎ ምግባር ለመተግበር አስበው የሚያነቡ አይደሉም፡፡ ሦስተኞቹ ወገኖች ግን መጽሐፍ ቅዱስን በእግዚአብሔር ፍቅር ውስጥ ሆነው የሚያነቡ ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች እያንዳንዷን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እግዚአብሔርን በማፍቀር ሆነው የሚያነቡ ናቸው(with Love of God)"ይለናል፡፡