ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
02/07/2004
ቅዱስ
ኤፍሬም በዚህ ጽሑፉ ላይ ቤተ-ክርስቲያን የሚለው እኛን ክርስቲያኖችን ነው፡፡ በእኛ ግንባር ላይ ስንጠመቅ የሥላሴ ስም
ተጽፎአል ስለዚህም የክርስቶስ
ቤተሰዎች ተሰኝተናል፡፡ በዚህ ስም ላይ ሌላ ስም መለጠፍ ወይም መጨመር ወይም መቀነስ ፈጽሞ የሚገባ ተግባር አይደለም፡፡
እንዲህ ማለት በክርስቶስ የተፈጸመልንን የማዳን ሥራ ዋጋ ማሳጣት ይሆናል፡፡ ምናልባት በቅዱስ ኤፍሬም ዘመን ቤተ ክርስቲያንን
በራስ ስም መጥራት ወይም ሌላ ተጨማሪ ስም መስጠት ወይም መቀነስ ታይቶ ይሆናል፡፡ በዚህም ዘመን በራሳቸው ስም ቤተ
ክርስቲያንን ከፍተው እንደግል ንብረታቸው ቆጥረው የሚኖሩ እንዳሉ ከወደ አሜሪካ ይሰማል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ለጭብጡ
መነሻ ነጥብ የሚያደርገው ቅዱስ ጳውሎስ “እያንዳንዳቹ ፡- እኔ የጳውሎስ ነኝ እኔስ የአጵሎስ ነኝ እኔ ግን የኬፋ ነኝ እኔስ
የክርስቶስ ነኝ ትላላችሁ፡፡ ክርስቶስ ተከፍሎአልን ጳውሎስስ ስለእናንተ ተሰቀለን ወይስ በጳውሎስ ስም ተጠመቃችሁን”
(1ቆሮ.1፡12)ብሎ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን የጻፈውን መልእክት መሠረት አድርጎ ሳይሆን አይቀርም፡፡
አንተ
በመንጎቹ ላይ የተሾምህ ካህን ሆይ ለጌታህ ሙሽራ የሆነችው ቤተክርስቲያን እነሆ!! እርሱዋን ከክፉ ሁሉ ጠብቃት፤
እርሱዋን በማባበል የራሳቸውን ስም ለመለጠፍ ከሚተጉትም ተኩሎች ጠብቃት፡፡ የእርሱዋ የሆነው የሙሽራው ስም በላይዋ
ላይ ታትሞአልና ሌላ ስም ለእርሱዋ በመስጠት ከሌሎች ጋር ታመነዝር ዘንድ አትፍቀድ፡፡ እርሱዋ የታተመችበት ስም በሩቁ ብእሲ
ስም አይደለምና በግንባሯ ላይ የታተመውን ስም በመጥራት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅድስ ማመኑዋን በይፋ ትገልጥ ዘንድ
አስተምራት፡፡ በሥላሴ ስም ትጠራ ዘንድ ያበቃሃት ጌታችን ሆይ! ስምህ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ የተመሰገነ ይሁን!!!