Saturday, March 10, 2012

ለቤተክርስቲያን መሪዎች የቅዱስ ኤፍሬም መልእክት






ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
02/07/2004
ቅዱስ ኤፍሬም በዚህ ጽሑፉ ላይ ቤተ-ክርስቲያን የሚለው እኛን ክርስቲያኖችን ነው፡፡ በእኛ ግንባር ላይ ስንጠመቅ የሥላሴ ስም ተጽፎአል ስለዚህም የክርስቶስ ቤተሰዎች ተሰኝተናል፡፡ በዚህ ስም ላይ ሌላ ስም መለጠፍ ወይም መጨመር ወይም መቀነስ ፈጽሞ የሚገባ ተግባር አይደለም፡፡ እንዲህ ማለት በክርስቶስ የተፈጸመልንን የማዳን ሥራ ዋጋ ማሳጣት ይሆናል፡፡ ምናልባት በቅዱስ ኤፍሬም ዘመን ቤተ ክርስቲያንን በራስ ስም መጥራት ወይም ሌላ ተጨማሪ ስም መስጠት ወይም መቀነስ ታይቶ ይሆናል፡፡ በዚህም ዘመን በራሳቸው ስም ቤተ ክርስቲያንን ከፍተው  እንደግል ንብረታቸው ቆጥረው የሚኖሩ እንዳሉ ከወደ አሜሪካ ይሰማል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ለጭብጡ መነሻ ነጥብ የሚያደርገው ቅዱስ ጳውሎስ “እያንዳንዳቹ ፡- እኔ የጳውሎስ ነኝ እኔስ የአጵሎስ ነኝ እኔ ግን የኬፋ ነኝ እኔስ የክርስቶስ ነኝ ትላላችሁ፡፡ ክርስቶስ ተከፍሎአልን ጳውሎስስ ስለእናንተ ተሰቀለን ወይስ በጳውሎስ ስም ተጠመቃችሁን” (1ቆሮ.1፡12)ብሎ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን የጻፈውን መልእክት መሠረት አድርጎ ሳይሆን አይቀርም፡፡
አንተ በመንጎቹ ላይ የተሾምህ ካህን ሆይ ለጌታህ ሙሽራ የሆነችው ቤተክርስቲያን እነሆ!! እርሱዋን ከክፉ ሁሉ ጠብቃት፤ እርሱዋን በማባበል የራሳቸውን ስም ለመለጠፍ  ከሚተጉትም ተኩሎች ጠብቃት፡፡ የእርሱዋ የሆነው የሙሽራው ስም በላይዋ ላይ ታትሞአልና ሌላ ስም ለእርሱዋ በመስጠት ከሌሎች ጋር ታመነዝር ዘንድ አትፍቀድ፡፡ እርሱዋ የታተመችበት ስም በሩቁ ብእሲ ስም አይደለምና በግንባሯ ላይ የታተመውን ስም በመጥራት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅድስ ማመኑዋን በይፋ ትገልጥ ዘንድ አስተምራት፡፡ በሥላሴ ስም ትጠራ ዘንድ ያበቃሃት ጌታችን ሆይ! ስምህ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ የተመሰገነ ይሁን!!!

ለእርሱዋ ወንድሞች የሆኑ ሐዋርያት ስለተሰጣት ስም ይቀናሉና ሌሎች ባዕድ ስሞችን ለእርሱዋ በመስጠት አታስቆጡአቸው፡፡ የሀሰት ስሞች ለእርሱዋ በመሰጠቱ ብቻ አይለደም የሚቆጡት በእውነተኞቹም በኬፋም ቢሆን በጳውሎስ ስም መጠራቱዋን አይፈቅዱምና ተጠንቀቅ፡፡ እርሱዋን ለክርስቶስ ያጩዋት ሐዋርያት እውነተኞች ናቸውና ለእርሱዋ የእርሱዋን የሙሽራዋን ስም ሰጡዋት፡፡ ነገር ግን ሐሳውያን ከሌሎች ጋር ታመነዝር ዘንድ የራሳቸውን ስም ለቤተክርስቲያን ይሰጡዋታል፡፡ የራስህን ስም ለቤተ ክርስቲያን በመስጠት ያከበርካት ፈጣሪያችን ሆይ! ለስምህ ክብር ምስጋና ይሁን!!
ወንድሞች ሆይ ማንም ቢሆን በግልጽ በመንጎቹ ግንባር ላይ የታተመውን መለያ ምልክት አያጥፋ ወይም ማንም በዚህ ስም ላይ ሌላ ተጨማሪ ስምን ወይም ተለዋጭ ስምን አያኑር፡፡ በቤተ ክርቲያን ላይ በታተመው ስም ላይ ሌላ ስም የሚጽፍ ወይም ይህን መልክት  የሚያጠፋ ወይም ሌላ ተለዋጭ ስም የሚሰጣት እርሱ ሌባ ነው፡፡ የራሱን ስም በመንጋው ላይ የሚጽፍ እርሱ ከክፉው ከሰይጣን ወገን  ነው፡፡  የክርስቶስ ስም በእርሱዋ ላይ ተጽፎ በግልጥ ይታይና ለእርሱዋ ሌላ ስምን የሚሰጡ ሁሉ ቤተ ክርስቲያንን አመንዝራ ያደርጋታል፡፡ የራሱን መንጎች በራሱ ስም መጥራት ያለበት እርሱ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ለእርሱ ለወደደን ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋና ይሁን ለዘለዓለሙ አሜን!!!

1 comment:

  1. Amen kale hiwot yasemaln edmi na tina yisetiln.

    ReplyDelete