በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
03/06/2000 ዓ.ም የተጻፈ
ቀኑ እንዴት ነጎደ! ውስጤን ፍርሃት ፍርሃት አለው መቼም ሰው ሳያውቀው ወደ እግዚአብሔር
መጣራቱ አይቀሬ ነው፡፡ አምላኩ ፊት ለፍርድ ሊቆም ነፍሱ ከሥጋው በተለየች ጊዜ ከትሞ ይኖርባት የነበረችውን ይህችን ግዙፍ ዓለም
እንደ ሕልም እንደቅዠት ሆና ትረሳዋለች፡፡ በተቃራኒውም ይህችኛዋም ዓለም እርሱን ፈጥና ለዘለዓለም ትረሳዋለች፤ ስም
አጠራርህም ከእነአካቴው ከሰው ሕሊና ይጠፋል፡፡ ወደ አምላካችን በሄድን ጊዜ ለዘለዓለም ከምንለያት ከዚህች ዓለም ሳለን ማወቅና መጠንቀቅ ያለንባቸውን
እውቀቶችንና መንፈሳዊ ተግባራት ከፊት ይልቅ ግልጥ ሆነው በሰዋዊ አእምሮአችን ከምናቀው በላይ የመላእክትን እውቀት ገንዘባችን በማድረግ
እናውቃቸዋለን፡፡ በፊቱ በቆምን ጊዜ እኛ በእርሱ ዘንድ የታወቅን፣ የጠጉራችንም ቅንጣት የተቆጠረች፣ በእርሱ ዘንድ የተራቆትን እንደሆንን
ይበልጥ ግልጥ ይሆንልናል፡፡ በዚህ ምድር ሳለን በእምነት የምንረዳቸውን እውነታዎች በዚያን ጊዜ በግልጥ እናያቸዋለን፡፡