Monday, August 13, 2012

የፍቅሩ ድልድይ (በቅዱስ ኤፍሬም)



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
07/12/2004
መግቢያ
በዚህ ርእስ ግሩም የሆነውን የቅዱስ ኤፍሬም መጽሐፍ ቅዱስን የመረዳት ጸጋውን እንመለከታለን ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ በኩል ሲናገር  የሰውን ተፈጥሮአዊ ጠባይ በመጠቀም ነበር ፡፡ በፈጣሪና በፍጡር መካከል ያለውን ልዩነት ቅዱስ ኤፍሬም ታላቅ ገደል ወይም ጥልቁ ጸጥታ ብሎ ይጠራዋል፡፡ እንደ ቅዱስ ኤፍሬም አስተምህሮ በሰው ላይ የሚታዩ ተፈጥሮአዊ ጠባዮችን ለራሱ በመስጠት በእርሱና በሰው መካከል ያለውን ሰፊ የሆነ ልዩነት ያጠበበው እግዚአብሔር ራሱ ነው፡፡ እንዲህ ማድረጉ ክብር ይግባውና ለሰው ልጆች ካለው ጥልቅ ፍቅር የተነሣ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ለሰው የሚሰጠውን መጠሪያና ጠባይ ለራሱ ተጠቅሞባቸው እናገኛቸዋለን፤ እንደ ቅዱስ ኤፍሬም የአጻጻፍ ዘይቤ ደግሞ እንደ ልብስ ለብሶአቸው እናገኛቸዋለን፡፡
በብሉይ ኪዳን በእኛ ምሳሌ በመገኘት ራሱን የገለጠልን እግዚአብሔር አምላክ የተመሰገነ ይሁን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር እንደሚሰማን ሊያሳውቀን ስለጆሮዎቹ ነገረን፤ እኛን እንደሚመለከተን ሊያስረዳንም ስለዐይኖቹ ጻፈልን፡፡ በዚህ መልክ በምሳሌአችን ተገልጦ እግዚአብሔር እኛን ይመክረናል ይገሥጸናል፡፡ እርሱ በባሕርይው ቁጣና ጸጸት የሌለበት አምላክ ሲሆን ስለእኛ ጥቅም እነዚህንም ግብሮች ለራሱ ሰጥቶ ተናገረን፡፡