Thursday, April 19, 2012

እናት



በወንድም ሸዋዓለም ፈቃዱ
12/08/2004

መነሻ ዳርቻ ፍጻሜ የሌለው፤
ጥንቱን የማላውቀው ፍጹም የማለየው፤
አለ አንዳች ስበት ከስሜት የጸዳ፤
ከእናት ያጣበቀ ከእናት የተቀዳ፡፡
እማዬ ፡- ያኔ… ያ…ኔ ክፉውን ከደጉ ያለየሁኝ ለታ፤
በቅጽበት ዐይን ያልተለየኝ ላፍታ፤
ከጡቶችሽ ምጌ ከልቤ ያኖርኩት፤
አንዳች ምሥጢር አለ እኔ ያልገለጽኩት፡፡
ካንቺ የሰረፀ ያ  ኃያሉ ፍቅርሽ ፤
ከየት ቋንቋ ላምጣ እንደምን ልግለጽሽ፡፡
እማ… እማዬ… እኔ ብቻ ሳልሆን እኔን የሚመስሉ፤
ሰው ሁነው ተፈጥረው በዓለም ዙሪያ ያሉ ፤
ስለእናት አዚመው ስለእናት ቢቀኙ፤
ዓለምን ቢዞሩ ገላጭ ቃል ቢያገኙ፤
አልሆነላቸውም ምንም ቢባዝኑ ፤
ምንም ቢፈትሹ የትም ቢኳትኑ፡፡
ስለዚህም መግለጫ ቃል ቢያጡ፤
በአንደነት በጋራ ዓለሜ ናት ብለው ለአንቺ ስም አወጡ፡፡
እኔስ የእኔ እናት፣ ውዴ የእኔ ሕይወት፣ ስላንቺ ምንም አልልም፤
ከቶም አልጽፍልሽም፤ ዝምታ እንጂ አንቺን ቃላት አይገልጽሽም፤
ስለአንቺ አላወራም አልዘምርልሽም፤
ፈጣሪ ሲፈጥርሽ አልፈጠረልሽም፤
በምድር የሚገኝ ገላጭ ቃል የለሽም፡፡

“…በተቀደሰው ተራራህ ማን ይኖራል?”(በቅዱስ ጀሮም)



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
12/08/2004
መግቢያ
ቅዱስ ጀሮም የላቲን አባቶች ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ሲሆን የታሪክ ጸሐፊ፤ የቅዱሳት መጻሕፍት ተርጓሚ፤ እና የቤተክርስቲያን ጠበቃዎች ከሚባሉት ውስጥ የሚመደብ ቅዱስ ነው፡፡ ለዛሬ ከእርሱ ሥራዎች ውስጥ የዳዊት መዝሙር 14ን ከሞላ ጎደል የተረጎመበትን ጽሑፍ ተርጉሜ አቅርቤላችኋለሁ፡፡
መዝሙር 14(15)
“የዳዊት መዝሙር”
1.      አቤቱ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል?
በተቀደሰውም ተራራህ ማን ይኖራል?
2.     በቅንነት የሚሄድ፣ ጽድቅንም የሚያደርግ፣
በልቡም እውነትን የሚናገር፡፡
3.     በአንደበቱ የማይሸነግል፣
በባልንጀራው ላይ ክፋትን የማያደርግ፣
ዘመዶቹንም የማይሰድብ፡፡
4.    ኃጢአተኛ በፊቱ የተናቀ፣
እግዚአብሔርንም የሚፈሩትን የሚያከብር፣
ለባልንጀራው የሚምል የማይከዳም፡፡
5.     ገንዘቡን በአራጣ የማያበድር፣
በንጹሑ ላይ መማለጃን የማይቀበል፡፡
እንዲህ የሚያደርግ ለዘለዓለም አይታወክም፡፡
 ጀሮም ትምህርቱን እንዲህ ይጀምራል፡- ከርእሱ እንደምንመለከተው “የዳዊት መዝሙር” ይላል፡፡ ዳዊት የክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡(ይህን አስመልክቶ የሰጠውን ትርጓሜ ወደፊት እጽፈዋለሁ) ከዚህ በተጨማሪ ግን ዘጸአትን ስናነብ እስራኤላውያን በዐሥራ ዐራተኛው ዕለት ከግብጽ ባርነት የተላቀቁበትን ዕለት ቀንዱ ያልከረከረ ጥፍሩ ያላረረ በግ እንዲሠው መታዘዛቸውን እናስታውሳለን፡፡(ዘጸአ.12፡6) በዐሥራ ዐራተኛው ቀን ጨረቃ ሙሉ በሆነችበት ዕለት ምድሪቱን በብርሃኑዋ በምታበራበት ጊዜ መሥዋዕቱን እንዲያቀርቡ እስራኤላውያን ታዘዋል፡፡ በዚህም በሙሉ ቅድስና ሕይወት ተገኝተን ከመሥዋዕቱ ልንቀበል እንዲገባን ያስተምረናል፡፡