Sunday, February 26, 2012

"ሕይወትም ቢሆን ሞትም ቢሆን..."


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
19/06/2004
እግዚአብሔር አምላካችን የፍጥረት ቁንጮ የሆነውን እኛን በሞትና በሕይወት ምሳሌ ፈጠረን፡፡ አዳምን በሞት ሔዋንን ደግሞ በሕይወት ምሳሌ ፈጠራት፡፡ እኛ ዘር እንሰጥና እሩጫችንን ስናበቃ ሴት ልጅ ግን በአካልዋ ውስጥ ለሰጠናት ዘር ሕይወትን በመስጠት ሕይወትን ትቀጥላታለች፡፡ እኛ ወንዶች ከሴቶች ይልቅ ሞትን ማሰብ በውስጣችን ስላለ የልጆቻችን ቀጣይ ሕይወት ሲያሳስበን ሴትን ልጅ ግን ሕይወት በእጁዋ ስለሆነ  ዕለታዊው የሆነው ነገር ያስጨንቃታል፡፡
 እኛ ወንዶች ዘርን ሰጥተን በሕሊናችን ይህችን ዓለም አሳልፈናት ስንሰናበታት፤ ሴት ልጅ ግን ለዚህች ዓለም ሕይወትን ሰጥታ ሕያዋን ልጆችን በመውለድ ዳግም እኛን በልጆቻችን ሕያዋን በማድረግ ሕይወትን እንድንኖራት ታደርገናለች፡፡ እኛ ሞትን አስበን ራእይን ለልጆቻችን ስናሰንቃቸው፤ ሴት ልጅ ግን ሞት በእርስዋ ውስጥ አይታሰብምና ለእነርሱ በሕይወት መቆየት ትታትራለች፡፡
ሞትና ሕይወት ፈጽመው የሚጣጣሙ ባይሆኑም እግዚአብሔር አምላክ አጣጥሞ ያውም በእኛ ተፈጥሮ ውስጥ ገለጣቸው፡፡ አዳም በሞት አርአያ አንቀላፍቶ ሳለ ሔዋንን አስገኛት፡፡ እርሱዋም ምድሪቱን ከእርሱ ባገኘችው ዘር በሕይወት ሞላቻት፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስም በሞቱ ቤተ ክርስቲያንን መሠረታት፤ እርሱዋም ከእርሱ ባገኘችው ዘር መንፈስ ቅዱስ ምድርን በሕያዋን ልጆቿ ከደነቻት፡፡
ጌታችን የሞት ምሳሌ የሆነውን የአዳምን ተፈጥሮ በሞቱ ሲያከብረው የሕይወት ምሳሌ የሆነውን የሴትን ተፈጥሮ ደግሞ በትንሣኤው አከበረው፡፡ ስለዚህም ለእኛ ለክርስቲያኖች ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው በዚህ ምድር መኖራችን  ጥቅም ነው፤ ከዚህ ዓለም ተለይተን ከክርስቶስ ጋር መኖርም ለእኛ እጅግ መልካም ነው፡፡(ፊል.1፡23-24) ለዚህም ይሆናል ይህ ሐዋርያ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች “ሁሉ የእናንተ ነው” ካለ በኋላ “… ዓለምም ቢሆን ሕይወትም ቢሆን ሞትም ቢሆን ያለውም ቢሆን የሚመጣውም ቢሆን ሁሉ የእናንተ ነው እናንተም የክርስቶስ ናችሁ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ነው”ማለቱ፡፡(1ቆሮ.3፡22-23)ድንቅ ነው!!!  

አጋፔ (Agape)



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
18/06/2004
(ስብከት ወተግሣጽ ከሚለው መጽሐፌ ተወስዶ የተብራራ)
ቃሉ ግሪክ ቃል ነው፡፡ ትርጉሙም ክርስቲያናዊ ፍቅር ``Charity`` (1ኛ ቆሮ 131-8) ማለት ሲሆን ይህ በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ የተገለጠ ፍቅር ነው፡፡ ቅዱስ አግናጥዮስ ዘአንጾኪያ ቅዱስ ሂፖሊተስ አጋፔን ከቅዱስ ቁርባን ጋር አገናኝተው ያስተምሩታል፤ መጽሐፉም ይህንን ይደግፋል፡፡ ይሁዳ ቁ.12 ላይ “በፍቅር ግብዣችሁ”ሲል ክርስቲያናዊ ፍቅርንና ቅዱስ ቁርባኑን በአንድነት አጣምሮ ሲገልጠው ነው፡፡ “ፍቅር” ያለው አጋፔ የተባለው ክርስቲያናዊ ፍቅርን ሲሆን “ግብዣችሁ” የተባለው ቅዱስ ቁርባኑ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ በእሑድ ወይም በስምንተኛው ቀን ይመሰላል፡፡ የክርስቲያን እሑድ እንደ ስምንተኛው ቀን ይቆጠራል፡፡ ምክንያቱም እሑድ የቀናት መጀመሪያ ናት፡፡ ክርስቲያን ደግሞ በክርስቶስ አዲስ ፍጥረትና በኩር ስለሚሆን ብኩርና ያገኘባት ያች ቀን ለእርሱ እንደ እሑድ ቀን ናት፡፡
ይህ ክርስቲያን በጥምቀቱ ከዚህ ዓለም እያለ በላይ በሰማያት ከትመው ከሚኖሩት ከቅዱሳን ነፍሳትና ቅዱሳን መላእክት ጋር መኖሪያውን ያደርጋል፡፡ እነርሱ ከምድራዊ ሥርዐት ውጪ እንደሆኑና ምድራዊው የሆነው የቀን ቀመር እንደማያገለግላቸው እንዲሁ ለዚህም ክርስቲያንም በአዲስ ተፈጥሮው ከእነርሱ ጋር ማኅበርተኛ ሆኖአልና ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እንግዲህ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል፡፡ ወደ ዕረፍቱ የገባ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ እርሱ ደግሞ ከሥራው አርፎአልና፡፡”(ዕብ.4፡9-10)እንዳለው ለእርሱም የቀን ቀመርና አቆጣጠር አያስፈልጉትም፡፡ ይህን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲያብራራው “ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፤ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም በደስታ ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፍት መላእክት ፣ በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኩራት ማኅበር የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር ፤ፍጹማንም  ወደ ሆኑት  ወደ ጻድቃን መንፈሶች፤ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገረው ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል” ብሎናል፡፡ (ዕብ.11፡22-24)