Friday, February 10, 2012

ነፍስ ለሥጋ ያቀረበችው ምስጋና



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
02/06/2004 

ነፍስ እንዲህ ብላ ሥጋን አመሰገነቻት፡፡ ሥጋዬ ሆይ እኔ ብቻ ሳልሆን መላእክትም አንቺን እጅግ ያከብሩሻል ያፈቅሩሻል፡፡ ምክንያቱም ባንቺ ነውና እነርሱ እርሱን መመልከታቸው፡፡ አስቀድሞ ግን ምንም እንኳ እነርሱ ረቂቃን ቢሆኑ ረቂቅ የሆነውን  እግዚአብሔርን ለማየት  አልተቻላቸውም ነበር፡፡ ስለዚህም በሰው አምሳል ተገልጦ ይታያቸው ነበር፡፡ አሁን ግን ከእናታችን የነሳውን ሰውነት ገንዘቡ አድርጎአልና እርሱን ለማየት በቁ፡፡ ስለዚህም ሥጋዬ ሆይ መላእክት አንቺን ያፈቅሩሻል ያመሰግኑሻል፡፡ እንደዲያማ ባይሆን እግዚአብሔርን እንዴት ሊያዩት ይችሉ ነበር? እኛም በእርሱ አባቱን ልንመለከት፣ መንፈስ ቅዱስም ሕይወታችን ሊሆን እንዴት ይችል ነበር? ሕመምተኞችስ እንዴት ወደ እርሱ ቀርበው የልብሱን ዘርፍ በመዳሰስ  ከሕመማቸው ይፈወሱ ነበር? እኛስ እንዴት የእርሱ የአካሉ ሕዋሳት ልንሆን እንችል ነበር? እንዲህ ባይሆን ኖሮ ይህ ሁሉ ባልተፈጸመልን ነበር፤ ምክንያቱም እርሱ እሳት ልብሱም እሳት ነውና፡፡ እርሱ የማይጨበጥና የማይዳሰስ ረቂቅ እንዲሁም ማንም በማይደርስበት ብርሃን ውስጥ የሚኖር ነውና፡፡ ወደ እርሱስ መቅረብ የሚቻለው ማን ነበር? እርሱ  የሚባላ እሳት ነውና፡፡