በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
28/10/2004
ክርስቲያኖች ሆይ ኑ ከቅዱስ ኤፍሬም ጋር መንፈሳዊ ቅኔን እንቀኝ፡፡ እርሱ ስለቅድስት ድንግል ማርያም እንዲህ ይላል “አዳም ለሔዋን እናትም አባትም እንደነበር እንዲሁ
ቅድስት ድንግል ማርያም ለልጁዋ ለወዳጁዋ እናትም አባቱም ሆነች፡፡” ከዚህ ተነስተን አዳም የሚለው መጠሪያ ለድንግልም የሚያገለግል እንደሆነ እንረዳለን፡፡
ስለዚህ አዳም ስንል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማለታችን እንደሆነ ሁሉ እንዲሁ አዳም ስንል ቅድስት ድንግል ማርያም
ማለታችንም ነው፡፡በእርግጥ ጥንትም አዳም የሚለው መጠሪያ ስም ለወንዱ ብቻ የሚያገለግል መጠሪያ ሰም አልነበረም “እግዚአብሔር
አዳምን በፈጠረበት ቀን ወንድና ሴት አድረጎ ፈጠራቸው ባረካቸውም፡፡ ስማቸውንም በፈጠረበት ቀን አዳም ብሎ ጠራቸው” ይላልና፡፡(ዘፍ.5፡2)
እነሆ አዳም የሚለው መጠሪያ ስም ለሴቶችም እንደሆነ እንረዳ ዘንድ ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ አዳም ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ እናትም አባትም ሆና አሳደገችው፡፡
ይህ ምሥጢር ሌላም እውነታን በውስጡ አዝሎ ይዟል፡፡ እርሱም፡- በክርስቶስ አምነን የእርሱ የአካሉ ሕዋሳት ለሆነውና በእርሱ አካል ለምንገለጠው ክርስቲያኖችም( ሮሜ.12፡5) ቅድስት ድንግል ማርያም እናትም አባትም መሆኑዋን እንረዳለን፡፡ ኦ ጌታችን
ሆይ!!! ይህ እንዴት ድንቅ የሆነ ምሥጢር ነው!!!