Wednesday, July 4, 2012

ዳግማዊቱ አዳም


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
28/10/2004
ክርስቲያኖች ሆይ ከቅዱስ ኤፍሬም ጋር መንፈሳዊ ቅኔን እንቀኝ፡፡ እርሱ ስለቅድስት ድንግል ማርያም እንዲህ ይላልአዳም ለሔዋን እናትም አባትም እንደነበር እንዲሁ ቅድስት ድንግል ማርያም ለልጁዋ ለወዳጁዋ እናትም አባቱም ሆነች፡፡” ከዚህ ተነስተን  አዳም የሚለው መጠሪያ ለድንግልም የሚያገለግል እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ስለዚህ አዳም ስንል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማለታችን እንደሆነ ሁሉ እንዲሁ አዳም ስንል ቅድስት ድንግል ማርያም ማለታችንም ነው፡፡በእርግጥ ጥንትም አዳም የሚለው መጠሪያ ስም ለወንዱ ብቻ የሚያገለግል መጠሪያ ሰም አልነበረም “እግዚአብሔር አዳምን በፈጠረበት ቀን ወንድና ሴት አድረጎ ፈጠራቸው ባረካቸውም፡፡ ስማቸውንም በፈጠረበት ቀን አዳም ብሎ ጠራቸው” ይላልና፡፡(ዘፍ.5፡2) እነሆ አዳም የሚለው መጠሪያ ስም ለሴቶችም እንደሆነ እንረዳ ዘንድ ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ አዳም ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ እናትም አባትም ሆና አሳደገችው፡፡ ይህ ምሥጢር ሌላም እውነታን በውስጡ አዝሎ ይዟል፡፡ እርሱም፡- በክርስቶስ አምነን የእርሱ የአካሉ ሕዋሳት ለሆነውና በእርሱ አካል ለምንገለጠው ክርስቲያኖችም( ሮሜ.12፡5) ቅድስት ድንግል ማርያም እናትም አባትም መሆኑዋን እንረዳለን፡፡ ኦ ጌታችን ሆይ!!! ይህ እንዴት ድንቅ የሆነ ምሥጢር ነው!!!

3 comments:

  1. ዳግማዊት ሄዋን ቢሉ ይሽላል

    ReplyDelete
  2. ምንም መሰረት የለለው ሃሳብ ብሎግ ማድረክ ጥሩ ኣይደለም

    ReplyDelete
  3. እርግጥ ነው በእኛ ዘንድ እናትነቱዋ ጎልቶ ይነገራል እንጂ አባትም ሆና ክርስቶስን ማሳደጉዋ እምብዛም አይነገረም፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ይህን አስመልክቶ"Just as Adam fills the role of father and mother for Eve so too does Mary for Christ." ይላል፡፡ “(St.Epherm)on commentary on Tatian's Diatessaron. page 61.” እንዲህ ሲል ከእርሱዋ ስለነሣው ሰውነት እንደሆነ ግልጽ ነው ወይም አዳም ለሔዋን የእናትነትን ቦታ እንደተካ ቅድስት ድንግል ማርያምም ምድራዊውን አባትነት ተክታ ጌታችንን ማሳደጉዋን የሚያስረዳ እንጂ ሌላ ትርጉም እየሰጠነው አይደለም፡፡ ነገር ግን እርሱ በባሕርይው የእግዚአብሔር አብ ልጅ ነው፡፡ በእርግጥም እግዚአብሔር አብ የባሕርይ አባቱ ስለመሆኑ ማንም ሊያጣው የማይገባ እውነት ነው፡፡ሆኖም እርሱን ያለወንድ ዘር ወይም ያለምድራዊ አባት አባትም እናትም ሆና የወለደችውና ያሳደገችው እርሱዋ ቅድስት እናታችን ናት፡፡ ልክ ሔዋን ከአዳም ብቻ እንደተገኘች ጌታችንም በሥጋ ልደት ከእርሱዋ ብቻ ተወለደ፡፡ ነገር ግን ወንድሜ ምንም መሠረት የሌለው ካልክ ጽንሰ አሳቡ የቅዱስ ኤፍሬም ነው እንጂ የእኔ አይደለም፡፡ እንዲህ ማለቱ ደግሞ ምክንያታዊ ሆኖ ነው፡፡ ይህንም ከላይ ለማስረዳት ሞክሬአለሁ፡፡ እኔም ከጽንሰ አሳቡ ተነስቼ የተረዳሁትንና መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ጠቅሼ ገለጥኩት፤ ቅዱስ ኤፍሬምና መጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ካልሆኑ በእርግጥ ትምህርቱ አንተ እንዳልከው መሠረት አልባ ነው፡፡ ለእኛ አዲስ የሆነ ነገር ግን ጥንት በቅዱሳን አባቶች የታወቀና የተነገረ አሳብ ባለማወቃችን ብቻ መሠረት የሌለው ማለት ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም አዎ ዳግማዊት ሔዋን ነች ይህ እኮ ከደም ከአጥንታችን የተዋሐደ ትምህርት ነው፡፡ የሚታወቀውን መድገም ስለምን ያስፈልጋል!!! የማናቀውን ነገር ግን እውነት የሆነውን ለአንባቢ ማድረስ እንዳለብኝ ግን ይሰማኛል፡፡

    ReplyDelete