Saturday, July 21, 2012

ለፍቅር መምህር የሆነ ፍቅር እና ወዳጄ ሆይ .....


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
14/11/2004
ጾታዊ ፍቅር በራሱዋ ንጽሕትና ቡርክት እንዲሁም ቅድስት ናት፡፡ በዚህ ፍቅር የወደድካትን ካገኘሃት፤ ይህች ፍቅር በልብህ ውስጥ ርኅራኄን፣ አክብሮትን፣ትዕግሥትን፣ አርቆ አሳቢነትን ስትዘራብህ ታገኛታለህ፡፡ ከአጣሃት ግን ከልብህ ስለማትወጣ እስከ ነፍስህ ህቅታ ድረስ በልብህ ሃዘንን ተክላ ትኖራለች እንጂ ፈጽማ አትጠፋም፡፡ወላጆች ሆይ ልጆቻችሁ ባለገንዘብ እንዲሆኑ ከመድከም ይልቅ ወደ እግዚአብሔር ባሕርይ የምታቀርባቸውን ይህችን ፍቅር በሕይወታቸው አግኝተዋት አእምሮአቸው ብሩህ ሆኖ ፍቅር የሆነውን አምላካቸውን እንዲያውቁትና እንዲያፈቅሩት ለዚህ ሕይወታቸው ትጉላቸው!!! እናንተ በእውነተኛይቱ ፍቅር ተጣብቃችሁ አንድ አካል ወደ መሆን የመጣችሁ ጥንዶች ሆይ! ንጽሕት፣ ቡርክት፣ ቅድስትና የእግዚአብሔር ፍቅር ፍጣሬ ብርሃን በሆነችው በዚህች ፍቅር ታግዛችሁራስን ለሚወዱት አሳልፎ እስከመስጠት ወደሚያደርሰውየክርስቶስ ፍቅር ታድጉ ዘንድ ምኞቴ ነው፡፡ ለዚህች ፍቅር እንደ መጥምቁ ዮሐንስ አዋጅ ነጋሪዎች ትሆኑም ዘንድ ምኞቴ ነው፡፡ አቤቱ አንተነትህን በዚህች በማንነታችን ውስጥ በጥልቀት በተከልካት ፍቅር እንድናውቅና በእንባ ሆነን በፍቅር እንድናመልክህ ይህችን ፍቅር በተፈጥሮአችን የሠራሃት አንተ ለዘለዓለም የተመሰገንክ ሁን፡፡ በዚህች ፍቅር ጠብን እንድናጠፋትና ፍቅርህን ለብሰን እንድንገኝ ጌታ ሆይ እርዳን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡